28/05/2026
†🌷 ፳፩ 🌷
።
†እንኩዋን የመገለጥ በዓል (ደብረ ምጥማቅ) በሰላም አደረሳችሁ።
†✝†🌷 ደብረ ምጥማቅ 🌷†✝†
የአርያም ንግሥት: የሰማይና የምድር እመቤት: የሰውነታችንም መመኪያ ቅድስት ድንግል ማርያም በዚሕች ዕለት በምድረ ግብፅ ለተከታታይ ቀናት ተገልጻለች::
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ: ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድረ ግብፅና ኢትዮዽያ በተሰደደ ጊዜ ከድንግል እናቱ: ከዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ዛሬ ደብረ ምጥማቅ በሚባለው ቦታ ላይ አርፎ ነበር:: ቦታውን ባርኮ ለዘለዓለም ያንቺ መገለጫ ይሁን ብሎም ቃል ኪዳን ገብቶላት ነበር::
ጊዜው በደረሰ ሰዓት ደብረ ምጥማቅ ተገድሞ የበርካታ መነኮሳት ቤት ሆነ:: እመቤታችንም በልጇ ፈቃድ ግንቦት 21 ቀን አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላት መጣች::
በዚያ ሕዝበ ክርስቲያንም: አሕዛብም ተሰብስበው ለ5 ቀናት ከእመ ብርሃን ጋር ይሰነብታሉ:: እንግዲህ ልብ በሉት:- እንኩዋን የአርያም ንግስት: የአምላክ እናቱ እመቤታችንን ይቅርና በዚሕ ዓለም ሰይጣን ቤቱ ያደረጋቸውን: የመዝናኛው ኢንዳስትሪ ዝነኛ ሰዎችን ለማየት የዘመናችን ሰው እንዴት እንደሚቸኩል::
እመቤታችንን በአካል መመልከት አይደለም ስሟን መጥራት ነፍስን ከሥጋ መለየት የሚችል ጣዕምና ደስታ አለው:: ባይሆን ይሔ ለሚገባውና ላደለው ብቻ ነው::
የደብረ ምጥማቅና የአካባቢዋ ሰዎች ከእመቤታችን ጋር የሚቆዩባቸው ቀናት የዘለዓለም የሕይወት ስንቅ የሚይዙባቸው ናቸው:: ፈልገው የሚያጡት: ጠይቀው የማይፈጸምላቸው ምንም ነገር አልነበረም:: ነቢያት: ሐዋርያት: ጻድቃን: ሰማዕታት: ደናግል: መነኮሳት: መላዕክትና ሊቃነ መላእክት ለድንግል ማርያም ሲሰግዱ ይታዩ ነበርና:: እመ ብርሃንም እየመላለሰች ትባርካቸው ነበር::
እነዚያ እርሷን ያዩ ዐይኖች: በፊቷ የቆሙ እግሮች ክብር ይገባቸዋል:: 5ቱ ዕለታት ሲፈጸሙ ሕዝቡ እመቤታችንን በዕንባ ይሰናበቷታል:: እመ ብርሃንም በብርሃን መስቀል ባርካቸው ከቅዱሳኑ ጋር ታርጋለች::
††† 🌷አባ መርትያኖስ 🌷†††
=>አባ መርትያኖስ በበርሃ ከ68 ዓመታት በላይ በቅድስና የኖሩ አባት ናቸው:: ሰይጣን እርሳቸውን ፊት ለፊት ተዋግቶ መጣል ቢያቅተው በዝሙት በተለከፉ ሴቶች ያስቸግራቸው ነበር::
አንድ ቀን አንዷ ሽቶ አርከፍክፋ በዝሙት ልትጥላቸው ብትል እግራቸውን እሳት ውስጥ ጨምረው እግራቸው እየተቃጠለ በሚወጣው ጠረን አጋንንትን አርቀዋል:: እሷንም በንስሃ መልሰው ለቅድስና አብቅተዋታል:: ጻድቁ ከፈተና ለመራቅ በ108 ሃገራት 108 በዓቶች የነበሯቸው ብቸኛ አባት ናቸው::
††† ለአባት እናቶቻችን የተገለጠች እመቤታችን ለእኛም በረድኤት ትገለጽልን:: ጣዕመ ስሟ በአንደበታችን: ጣዕመ ፍቅሯ በልባችን ይደርብን:: †††
=>ግንቦት 21 ቀን የሚከበሩ
ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ምጥማቅ (የእመቤታችን መገለጥ)
2.አባ መርትያኖስ ጻድቅ (በዝሙት ላለመሰናከል እግራቸውን በእሳት ያቃጠሉ አባት)
3.ቅዱስ አሮን ሶርያዊ
4.ቅዱስ አሞጽ ነቢይ
=>ወርኀዊ በዓላት
1.አበው ጎርጎርዮሳት
2.አቡነ ምዕመነ ድንግል
3.አቡነ አምደ ሥላሴ
"የምድር ባለጠጐች አሕዛብ በፊትሽ ይማለላሉ::
ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብሯ ነው::
ልብሷ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው::
በሁዋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ . . .
በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ::
በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ:: ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ:: " (መዝ. 44:12-17)
✝ ከበዓሉ በረከትም ያድለን !! ✝
🌹< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >🌹
27/05/2026
፳
ግንቦት ሃያ በዚህች ቀን የከበረ ጻድቅ የኢትዮጵያ አረፈ፣የሀገረ ቶና የከበረ አረፈ፣ ከአባቶች መምህራን ዐሥራ ስድስተኛ የሆነ በደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት ሆኖ የተሾመ የከበረ አባት አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
(መናኙ ንጉሠ ኢትዮዽያ)
ግንቦት ሃያ በዚህች ቀን የከበረ ጻድቅ የኢትዮጵያ ንጉሥ ካሌብ አረፈ። ይህ ቅዱስ እግዚአብሔርን የሚፈራውና በፍጹም ልቡ የሚወደው ሃይማኖቱም የቀና ነው።
በናግራን አገር ያሉ ክርስቲያኖችን አይሁድ እንደሚገድሏቸው በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ መንፈሳዊ ቅናትንም ቀና። ከዚህም በኋላ ተነሣ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ገብቶ በመሠዊያው ፊት ቆመ ዐይኖቹንም ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ ብሎ ጸለየ ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ሆይ የፍጥረት ሁሉ ጌታ የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠርህ መላእክት ሁሉ አእላፈ አእላፋት አንተን የሚያመሰግኑህ ለአንተም የሚገዙ ዐይኖቻቸው ብዙ የሆነ ኪሩቤል ክንፎቻቸው ስድስት የሆነ ሱራፌልም ጽኑዕ ክቡር ልዩ ፍጹም አሸናፊ እግዚአብሔር በቅዱሳን የሚመሰገን እያሉ ያለማቋረጥ የሚያመሰግኑህ ፣ ብርሃንን እንደ ልብስ የሚጐናጸፍ የክብር ባለቤት ለሆነ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባቱ እግዚአብሔር ሆይ የአማልክት አምላክ የጌቶች ጌታ የጠፉ በጎችን ይመልሳቸው ዘንድ ልጅህን ይኸውም ቃልህ ነው በፈቃድህ የላክኸው አንተ ነህ።
ተናጋሪ በግ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳትለይ ከሰማይ የወረድክና ስለ እኛ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው የሆንክ ከጨለማም ከድንቁርናም አውጥተህ ወደ ብርሃን ወደ ሕይወት ወደ ዕውቀት የመራኸን።
አሁንም ከሀዲ ወንጀለኛ ፊንሐስ የቤተ ክርስቲያንን ልጆች እንደ በጎች በማረድ እንደ ገደላቸው በእሳትም አቃጥሎ የወገኖችህንና የርስትህን ልጆች እንዳጠፋቸው እይ። እነሆ አብ ሆይ እኔ አመንሁብህ በአንድ ልጅህም በሕያው ቅዱስ መንፈስህም በመሠዊያህ ክብርም ተማፅኛለሁ በሃይማኖትህም ጸንቼአለሁ እነሆ ስለ አምልኮትህና ስለ ምእመናን ወንድሞቼ ስለ ቀናሁ በአንድ ልጅህ መስቀል ጠላቶችህን ልዋጋቸው እወጣለሁና ከአለኝታዬ እንዳታሳፍረኝ የማያውቁህም አምላካቸው ወዴት ነው እንዳይሉ።
ስለ በደሌና ስለ ኃጢአቴም ጸሎቴን የማትሰማ ልመናዬንም ንቀህ የምትተው ከሆነ በዚሁ ቦታ ብትገድለኝ ይሻለኛል። አቤቱ መሐሪ ይቅር ባይ ርኅሩህ ርስትህ የሆኑ ምእመናንን በከሀድያን ጠላቶችህ እጅ አሳልፈህ አትስጥ። እኛ ወገኖችህና የርስትህ መንጋዎች ስለሆን ለአንተም ምስጋና እናቀርባለን ምስጋና ገንዘብህ ነውና ለዘላለሙ።
ከዚህም በኋላ ንጉሥ ካሌብ ከሀገረ መንግሥቱ ወጥቶ ሔደ የናግራንን ሀገር ያጠፉአት አይሁድን ገደላቸው ብዙ ተአምራትም አድርጎ ስለ አደረገለት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ሀገረ መንግሥቱ በታላቅ ክብር በታላቅም ደስታ ተመለሰ።
ለእግዚአብሔር ምን ዋጋ እከፍለዋለሁ ለጌትነቱና ፍጹም ለሆነ ገናናነቱ መባ አድርጌ ነፍሴንና ሥጋዬን ከማቀርብለት በቀር አለ። ከዚህም በኋላ ይህን ዓለም ንቆ መንግሥቱንም ትቶ ወጣ ደጋጎች መነኰሳት ወደሚኖሩበት ወደ አባ ጰንጠሌዎን በተራራ ላይ ወደ አለ ገዳም እስከ ደረሰ በእግሩ ሔደ። ወደ ዋሻ ውስጥም ገብቶ ሰውም እንዳያየው የዋሻውን በር ዘግቶ በዚያ ውስጥ ኖረ ከዚያችም ወጥቶ ዳግመኛ ዓለምን እንዳያይ ማለ።
ከእርሱ ጋራም ያገባው ዕቃ የለም ከምንጣፍ ከሸክላ ጽዋ ከለበሳት የምንኲስና ልብስ በቀር ምግቡም አምባሻና ጨው የሚጠጣውም ውኃ ነው። የክብር ባለቤት ከሆነ ከእግዚአብሔር ቃል መቃብር መስኮት ላይ ይሰቅልለት ዘንድ የኢየሩሳሌሙን ኤጲስቆጶስ አባ ዮሐንስን እየለመነው ዋጋው ብዙ የሆነ የነገሠበትን ዘውድ ላከ።
ወደ ዋሻውም ከገባ በኋላ ከማንም ጋራ አልተነጋገረም እግዚአብሔርንም ደስ አሰኝቶ በፍቅር አንድነት አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ዕለት የሀገረ ቶና የከበረ አባ አሞንዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ጎልማሳ ሁኖ ሳለ አባ እንጦንዮስ ወደ ምንኩስና ሲጠራው ራእይን አየ። በነቃም ጊዜ ተነሥቶ ወዲያውኑ ወደ አባ ኤስድሮስ ሔደ ከእርሱም አስኬማን ለብሶ እያገለገለውም በእርሱ ዘንድ ኖረ።
ከዚህ በኋላም ወደ ደብረ ቶና ተመልሶ ለራሱ በዓትን ሠራ በታላቅ ገድልም ተጠምዶ በቀንም በሌሊትም ተጋደለ። ሰይጣንም በእርሱ ላይ ቀንቶ በሴት መነኲሲት አምሳል ወደርሱ መጣ የበዓቱን ደጃፍ በአንኳኳ ጊዜ ከፈተለትና ገባ ቅዱሱም ተነሥተን እንጸልይ አለው ያን ጊዜ ተንኰሉን ገለጠ መልኩም እንደ እሳት ላቦት ሆነ ቅዱሱንም እኔ ታላቅ ጦርነት አመጣብሃለሁ አለው።
ከዚህም በኋላ መልኳ ውብ ወደ ሆነ ወደ አንዲት ወጣት ሴት ሰይጣን ሒዶ አነሣሣት። ቅዱስ አሞንዮስን ከእርሷ ጋራ በኃጢአት ልትጥለው ቀጭን ልብሶችን ለብሳ ወደ ርሱ በምሽት ጊዜ ደረሰች።
እንዲህም እያለች ደጃፉን አንኳኳች እኔ መጻተኛ ሴት ነኝ መንገድንም ስቼ በምሽት ጊዜ ከዚህ ደረስኩ አራዊትም እንዳይበሉኝ በውጭ አትተውኝ እግዚአብሔርም ስለ እኔ ደም እንዳይመራመርህ።
በከፈተላትም ጊዜ የሰይጣን ማጥመጃው እንደ ሆነች የላካትም እርሱ እንደሆነ አወቀ በአምላካውያት መጻሕፍት ቃልም ገሠጻት ለኃጥአን ስለ ተዘጋጀ የሲኦል እሳትም አስገነዘባት ሁለተኛም ለጻድቃን ስለ ተዘጋጀ ፍጹም ተድላ ደስታ ነገራት።
ያን ጊዜም የሚላትን ታስተውለው ዘንድ እግዚአብሔር ልቧን ከፈተላት። መልካሙንም ልብስ ከላይዋ አውጥታ ጣለች ከእግሮቹ በታችም ሰገደች ነፍሷንም ያድን ዘንድ በማልቀስ ለመነችው። የጠጉር ልብስም አለበሳት ራስዋንም ተላጭታ በገድል ሁሉ በብዙ ትሩፋትም ተጠመደች በቀንም በሌሊትም ዐሥራ ሁለት ጊዜ የምትጸልይ ሁናለችና በየሁለትና በየሦስት ቀንም ትጾማለች።
ሰይጣንም በአፈረ ጊዜ በመነኲሴ ተመስሎ በየአንዳንዱ ገዳም ሁሉ በመግባት እያለቀሰና እያዘነ እንዲህ አላቸው በአባ አሞንዮስ ቤት ሴት አለችና እርሱ ከታላቅ ገድል በኋላ የአንዲትን ሴት ፍቅር ወዶአልና እርሷም በእርሱ ዘንድ በበዓቱ ውስጥ ትኖራለች እነሆ መነኰሳትን አሳፈራቸው አስኪማውንም አጐሳቈለ።
የመላእክት አምሳል የሆነ ጻድቁ አባ ዕብሎ ያን ጊዜ ተነሣ አባ ዮሴፍንና አባ ቦሂንም ከእሱ ጋራ ወሰዳቸው። ወደ ቅዱስ አሞንዮስ ገዳም ደብረ ቶና ደረሱ ደጃፉንም በአንኳኩ ጊዜ ያቺ ሴት ወደ እሳቸው ወጣች እርስ በእርሳቸውም ያ መነኲሴ የነገረን ዕውነት ነው ተባባሉ።
የከበረ አሞንዮስም ሳድዥ ብሎ ስም አውጥቶላታል ይህም የዋሂት ማለት ነው። ገብተውም ጸሎት አድርገው የእግዚአብሔርንም ገናናነት እየተነጋገሩ እስከ ምሽት ተቀመጡ።
አባ አሞንዮስም አምባሻ እየጋገረችልን ነውና ተነሡ ሳድዥን እንያት አላቸው። በገቡም ጊዜ በሚነድ የእሳት ምድጃ ውስጥ ቆማ እጆቿም ወደ ሰማይ ተዘርግተው ስትጸልይ አገኙዋት። አይተውም ስለዚህ ድንቅ ሥራ እጅግ አደነቁ የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት። ከዚህ በኋላም አቅርባላቸው በሉ።
በዚያቺም ሌሊት መልአክ ስለ አባ አሞንዮስና ስለ ሳድዥ ገድላቸውን ለአባ ዕብሎ ነገረው ወደዚህም ዛሬ ያደረሳችሁ እግዚአብሔር ነው የሳድዥን ዕረፍት እንድታዩ አላቸው።
ሦስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ የሚያስጨንቅ የሆድ ዝማ ታመመች በእግዚአብሔርም ፊት አንዲት ስግደትን ሰገደችና በዚያው ነፍሷን ሰጠች መልካም አገናነዝም ገንዘው ቀበሩዋት።
አባ አሞንዮስም ትሩፋቷን ሊነግራቸው ጀመረ እርሷ በእርሱ ዘንድ ዐሥራ ስምንት ዓመት ስትኖር ከቶ ፊቷን ቀና እንዳላደረገች እርሱም ደግሞ ፊቷን እንዳላያት ምግባቸውም አምባሻና ጨው እንደሆነ። ከጥቂት ቀን በኋላም አባ አሞንዮስ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን ከአባቶች መምህራን ዐሥራ ስድስተኛ የሆነ በደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት ሆኖ የተሾመ የከበረ አባት አባ በትረ ወንጌል አረፈ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ እንደ መላእክት ንጽሕናን የለበሰ ትሕትናን ቅንነትን የሚወድ ነበረ።
የምንኵስናንም ልብስ ከለበሰ በኋላ መልካም ገድልን ተጋደለ በክርስቶስ መንጋ ላይም ጠባቂ ሆኖ ተሾመ ከዚያም በኋላ በበጎ እርጅና አረፈ።
† ግንቦት 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አፄ ካሌብ (መናኙ ንጉሠ ኢትዮጵያ)
2.ቅዱስ አሞንዮስ ገዳማዊ (ታላቁ አሞኒ ዘቶና)
3.ቅድስት ሳድዥ የዋሂት
4.አባ ሖር ጻድቅ
5.አባ ዳርማ ገዳማዊ
6.ቅዱስ ዘካርያስ አንጾኪያዊ
7.አባ በትረ ወንጌል ዘደብረ ሊባኖስ
† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
2.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
3.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
( )
26/05/2026
፲፱
ግንቦት ዐሥራ ዘጠኝ በዚህች ዕለት
የዓለም ብርሃን የሆነ አባ ዮሴፍ አረፈ፣ የከበረ አባት መታሰቢያው ነው፣ የከበሩ አባት ዕረፍታቸው ነው፣በዚህችም ቀን የአቡነ #ዮሴፍ ዘአክሱም ልደታቸውና ዕረፍታቸው ነው፣ ከአባ መቃርስ ገዳም ቅዱስ አባት ቀሲስ ይስሐቅ አረፈ፣ኃይለኛ ተጋዳይ ቅዱስ ኤስድሮስ በሰማዕትነት አረፈ።
ግንቦት ዐሥራ ዘጠኝ በዚች ቀን ከአባ መቃርስ ገዳም ቅዱስ አባት ቀሲስ ይስሐቅ አረፈ።
ይህም አባት ከምሥር ከታናናሽ ቦታዎች ከአንዲት ቦታ ነው ወላጆቹም ድኆች ሲሆኑ ግን በበጎ ስራ ባለጸጎች ናቸው፤ አረጋውያን መነኰሳትም የእጅ ስራቸውን ሊሸጡ ወደ ምሥር በሄዱ ጊዜ ተከትሏቸው ወደ አስቄጥስ ገዳም መጥቶ ሲአገለግላቸው ኖረ፤ በቀንበራቸውም ተጠምዶ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ በዘመኑም ሁሉ ከቶ ምንም ጥሪት አላደረገም፤ እንደ አባቶቻችን ሁለት ልብሶችን ለምን አልገዛህም ሲሉት እርሱም እኔ እስከ ዛሬ ሕዝባዊ ነኝ በዓለም ሳለሁም ሁለት ልብስ የለኝም ነበር ብሎ ይመልስላቸዋል።
ሁለተኛም አባቶቻችንም እኮ ሰሌንና ማቅ ይለብሳሉ ለእኛም አንድ ልብስ ይገባናል ይህ አይበቃንምን አላቸው፤ ሁልጊዜ የሚያለቅስ ሆነ ለምን ታለቅሳለህ ብለው በጠየቁት ጊዜ ወላጆቼ ሙተውብኝ ድኃ አደግ አድርገውኛልና ይላቸዋል፤ ከምግቡም የማዕጠንት አመድ ጨምሮ እየበላ ብዙ ዘመናት ኖረ።
ከዚህ በኋላ ጭንቅ በሆነ ደዌ ተይዞ በታመመ ጊዜ ከወንድሞች አንዱ ምግብ ሰርቶ አመጣለት፤ እርሱም ከቶ አልቀመሰም ያም ወንድም ይህ ጥሩ ምግብ ነው ለበሽታህም መድኃኒትነት አለውና ብላ ብሎ ብዙ ለመነው፤ እርሱም ወንድሜ ሆይ እመነኝ እኔ በዚህ ደዌ ውስጥ ሠላሳ ዓመት እኖር ዘንድ እወዳለሁ ብሎ መለሰለት፤ በዕድሜውም በሸመገለ ጊዜ ትሩፋቱና ጽድቁም በበዛ ጊዜ ቅስና ይሾሙት ዘንድ አረጋውያን ተሰብስበው ተማከሩ።
እርሱም ከእርሳቸው ሸሽቶ ከተዘራ ማሳ ውስጥ ገብቶ ተሠወረ፤ እርሱንም እየፈለጉ ዞሩት አላገኙትም ያቺንም ማሳ አልፈው ከዳርዋ ተቀመጡ ጥቂት ሊያርፉ፤ ከእርሳቸውም ጋር አህያ ነበረ ወደ ማሳውም ሩጦ ገብቶ ይህ አባት በተሸሸገበት ቦታ ቆመ፤ አህያውን ሊያስወጡትም በገቡ ጊዜ ያንን አባት አገኙት፤ ደግሞ እንዳይሸሽ ሊአሥሩት ፈለጉ አሁንስ ዐውቄዋለሁ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ አላቸው ከዚያም አብሮአቸው ሒዶ ቅስና ሾሙት።
ከዚህ በኋላም ተጋድሎውንና ለአረጋውያን መታዘዙን ጨመረ ወጣቶችንም በጎ ሥራ ያስተምራቸዋል ሰምታችሁ የምትታዘዙ ሁኑ ከትሩፋት ሁሉ ይህ ይበልጣልና አላቸው፤ የሚያርፍበትም ጊዜ ሲደርስ ከእርሱ በኋላ የሚሠሩትን እንዲአስተምራቸው በዚያ ገዳም ያሉ ጎልማሶች በጠየቁት ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ በገዳሙ ውስጥ ጸንታችሁ እንድትኖሩ እኔ ስሠራ ስታዩኝ እንደነበረ እናንተም እንዲሁ በፈቃዳችሁ ሥሩ፤ እኛ አባቶቻችን በአረፉ ጊዜ አዝነን አልቅሰን ነበር እንደሚሠሩትም በሠራን ጊዜ ከእነርሱ በኋላ ተጽናንተን በገዳም የምንኖር ሆን። ይህንንም እያለ በፍቅር በሰላም አረፈ የሕይወት አክሊልንም አገኘ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ጸሎት ይማረን በረከቱም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
በዚችም ቀን ኃይለኛ ተጋዳይ ቅዱስ ኤስድሮስ በሰማዕትነት አረፈ፤ ይህም ቅዱስ ከእስክንድርያ አገር ከከበሩ ከቤተ መንግሥት ወገኖች ውስጥ ነው አባቱም በብዙ ሠራዊት ላይ የተሾመ መኰንን ነው፤ ስሙም በደላዖን ነው የእናቱም ስም ሶፍያ ነው ሁለቱም ከክርስቲያን ወገን ናቸው ይህንንም ቅዱስ በወለዱት ጊዜ ኤስድሮስ ብለው ሰየሙት።
ከብዙ ወራት በኋላም ከሀዲ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ የሚያደርገውን የኃጢአትና የበደልን ብዛት በአየ ጊዜ እርሱ ከመንግሥት ታላላቆች ውስጥ ስለሆነ ምስፍናውን ትቶ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋራ ገለል አለ፤ ስለ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጻተኞች በመሆን ከዚህ ዐላዊ ንጉሥ ፊት ሸሽተው ሳሙኤል ከሚባል ሰው ዘንድ ተሰባስበው በገዳም ተቀመጡ።
ከዚህ በኋላም ለጣዖታት እንዳይሰግዱ ከንጉሡ ሸሽተው ስለተሠወሩ ከሀድያን መጥተው በንጉሡ ዘንድ ነገር ሠሩባቸው። ወዲያውኑ አምስት መቶ ጭፍራ ልኮ ከፊቱ አስቀረባቸው፤ ከእርሱ ዘንድ በመገለላቸውም ንጉሥ ጠየቃቸው እነርሱም እንዲህ አሉት፤ የክብር ባለቤት ክርስቶስን በተውከው ጊዜ ተውንህ ታላቅ ስንፍና አድርገህ ስተሃልና፤ በሰማ ጊዜም ተቆጥቶ የበደላዖንን አንገት ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም አገኘ፤ ቅዱስ ኤስድሮስን ግን ይመከር እንደሆነ ብሎ አሠረው ያንጊዜ ዐሥራ ሁለት ዓመቱ ነበር።
ከጥቂት ቀን በኋላም በአንገቱ የብረት ዛንጅርና ገመድ አስገብተው ከንጉሥ ፊት አቀረቡት፤ ንጉሡም አልፈራህምን ልብህስ ለመመለስ አልመከረምን ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም እኔ የቀናች ሃይማኖቴን ትቼ ወደ ስሕተት አልመለስም አለው፤ ያን ጊዜ አራቁተው ከምሰሶ ላይ ሰቅለው ደሙ እንደ ውኃ እስቲወርድ እንዲጨምቁት ንጉሥ አዘዘ፤ እናቱ ሶፍያም ከደሙ ወስዳ በንጉሡ ፊት ላይ ረጨች፤ እንዲህም አለችው ከሰው ሁሉ አንተ የተረገምክ ነህ እንዲሁ እኅቱ አፎምያም ደንጋዮችን አንሥታ ንጉሡንና መኳንንቶቹን ወረወረችባቸው፤ ንጉሥም ተቆጣና ከወገባቸው መካከል እንዲቆርጧቸው አዘዘ ቆርጠዋቸውም ምስክርነታቸውን ፈጸሙ አክሊልንም አገኙ።
ቅዱስ ኤስድሮስም ተሰቅሎ ሳለ በእናቱና በእኅቱ ላይ የሆነውን ይመለከት ነበር በወገቡም ላይ የእሳት ፍም ደፉበት ደግሞም ሆዱን ሠንጥቀው አንጀቱን አወጡ፤ በተራራ ላይም ጣሉት የሰማይ ወፎችና የዱር አራዊት አልቀረቡትም፤ መድኃኒታችንም ከሞት አስነሥቶ እንደ ቀድሞ ሕያው አደረገው።
ከዚያም ሒዶ በንጉሡ ፊት ቆመ ንጉሡም ከብረት ዐልጋ ላይ አውጥተው ከበታቹ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ፤ ሁለተኛም በብረት ላይ አስተኝተው አንጀቱ እስቲፈስ ድረስ ፈጩት ከዚህም መድኃኒታችን አስነሣው፤ ደግሞም ሁለተኛ ከስምንት መቶ ነፍስ ጋር ሰቀሉት ያንጊዜም መድኃኒታችን አድኖ አስነሣው።
ንጉሡም አይቶ በበሬ ቅርጽ በተሠራ ብረት ውስጥ አሥረው በላዩም ድኝና ዝፍት ጨምረው ከበታቹ እሳት እንዲአነዱ አዘዘ፤ ከጥቂት ቀን በኋላ ራሱን እንዲቆርጡት አዝዞ ቆረጡት ያንጊዜም ጌታችን ከሞት አነሣው እነሆ ሲያስነሣው ሦስተኛው ነው፤ ደግሞ ከዚህ በኋላ እጅግ ከባድ የሆነ ደንጊያ በአንገቱ አሥረው ወደ ባሕር ጣሉት ወዲያውኑ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል አውጥቶ ከንጉሡ ፊት አደረሰው።
ንጉሡም በከተማ መካከል እንዲሰቅሉት አዘዘ እንደዚህም ተሰቅሎ ሞተ፤ የክብር ባለቤት ጌታችንም አስነሣው ይህም ሲያሥነሣው አራተኛ ጊዜ ነው፤ ከዚህም ለአንበሶች ጣሉት እግዚአብሔርም ነቢይ ዳንኤልን እንዳዳነ አዳነው።
ከዚህም በኋላ በየጥቂቱ ቆራርጠው እንዲከትፉትና በእንቅብ ሰብስበው ወደ ባሕር እንዲጥሉት አዘዘ አሽከሮቹም እንዱሁ አደረጉ፤ ያን ጊዜም የክብር ባለቤት ጌታችን ከሚካኤልና ከገብርኤል ጋራ መጥቶ በባሕሩ ዳር ቆመ ከዚያም አውጥቶ አስነሣው፤ ያለ ምንም ጉዳት ይህም ከሞት ሲያስነሣው አምስተኛ ነው።
ንጉሡም በአፈረና የሚያደርገውም በተሳነው ጊዜ ከወገኖቹ ጋራ ተማክሮ በዚያ ያሠቃዩት ዘንድ እጅና እግሩን አሥሮ ወደ ሰሎንቅያ ሀገር ላከው፤ የሰሎንቅያ አገር ገዥም አስቀድሞ ስለ ሚያውቀው ከቅዱስ ኤስድሮስ ጋራ ቸርነትን ርኅራኄን አደረገ።
ንጉሡም ሰምቶ ተቆጣ ያንን መኰንንም እንዲአመጡት አዘዘ፤ ቅዱስ ኤስድሮስንም ወደ እርሱ መልሶ በእሥር ቤት በረኃብና በጽምዕ አኖረው ቅዱሱም በእሥራቱ መጠን ታላላቅ ድንቆች ተአምራትን እያደረገ በሽተኞችን ሁሉ አዳነ።
በዚችም በግንቦት ዐሥራ ዘጠኝ ቀን በስድስት ሰዓት ከከተማ ውጭ እንዲሰቅሉት ንጉሥ አዘዘ፤ አየርም መላእክትን ተመላች የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ብዙዎች ቃል ኪዳኖችን ከእርሱ ጋራ አደረገ፤ ያን ጊዜም ነፍሱን አሳለፈ፤ በማይጠፋ መንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊላትን ተቀበለ በተጋድሎ የኖረባቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመቶች ናቸው።
በዚችም ቀን ከቅዱስ ኢስድሮስ ጋራ ስምንት መቶ አምስት ሺህ ሰባት ሰዎች በሰማዕትነት ሞቱ በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
በዚችም ዕለት የዓለም ብርሃን የሆነ አባ ዮሴፍ አረፈ፤ ይህም ቅዱስ ያዩትና የሰሙት እስቲአድንቁት ድረስ በአባቱ ቤት ሳለ የዚህን ዓለም ጥበብ ሁሉ ተማረ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት ተረጐመ ከዚህም በኋላ ዲቁና ሾሙት፤ የነፍሱንም ድኅነት እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ ብርሃናዊ መልአኩን ሚካኤልን ላከለትና ዮሴፍ ሆይ ይህን ኃላፊውን ዓለም ትወደዋለህን? አስጸያፊ አይደለምን በውስጡም ያለው ሁሉ አለው።
ከዚያችም ጊዜ ጀምሮ እርሱ የመረጠውን መንገድ ይመራው ዘንድ እግዚአብሔርን እየለመነ ጾምና ጸሎትን ጀመረ ከወለቃ አውራጃም ስሙ አባ ዘካርያስ የሚባል ነበረ እርሱም ለዮሴፍ ዘመዱ የሆነ በጭልታም ዮሴፍን ወስዶ የምንኲስና ልብስ አለበሰው ወደ ትግራይ ምድርም ወሰደውና በዚያ ተግባረ እድ ለምንኲስና ሥራ የሚገባ ጽሕፈትን ስፌትን ተማረ።
ከዚህም በኋላ ወደ በረሀ ዱር ገብተው የእንጨት ፍሬ እየበሉ ከዝኆኖች ከአንበሶችና ከዘንዶዎች እየተፈተኑ በየአይነቱ በሆነ ተጋድሎ በመድከም ኖሩ፤ በጽድቃቸውም ኃይል ብዙ ተአምራትን አደረጉ አባ ናትናኤልም የጋለ ምንቸት በመሐል እጁ ይዞ በመነኰሳቱ ፊት ዞረ፤ አባ ዮሴፍም የሚያበስሉበት ማሰሮ በተሰበረ ጊዜ ወጡ ሳይፈስ አገናኝቶ እንደ ቀድሞው አደረገው፤ ገብር ኄርም ሕዝባዊ ሲሆን በሞተ ጊዜ ሊአጠምቁት ሲሉ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ኤጲስቆጶስነት ሹሞኛልና እኔ በእጄ አጠምቃችኋለሁ አላቸው፤ እሊህም ቅዱሳን የትሩፋታቸውንና የጽድቃቸውን የአማረ ሥራቸውን አሳዩ።
ከዚህም በኋላ አባ ዮሴፍን ወደ ጳጳስ ወሰዱትና ቅስና ተሾመ፤ አባ ዘካርያስም በአረፈ ጊዜ አባ ዮሴፍ ወደ ሌላ ገዳም ሒዶ ሳይቀመጥ ቁሞ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ጾመ፤ ከድካም ጽናትም በወደቀ ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ አነሣው፤ ሁለተኛም ከገደል አፋፍ እጁን ዘርግቶ ሳይሰበስብ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ቆመ፤ ሰይጣንም መጥቶ ወደ ቆላ ወረወረው የመላእክት አለቃ ሚካኤልም ተቀብሎ ወደ መቆሚያው መለሰው፤ ደግሞም ከደንጊያ ዋሻ ውስጥ ገብቶ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ያለ መብልና ያለ መጠጥ ኖረ፤ ሰይጣናትም ወደርሱ እየመጡ በየራሳቸው ምትሐት በማሳየት ያስፈራሩት ነበር መላእክትም ያበረቱትና ያጸኑታል፤ ናላው በአፍንጫው እስቲፈስ ድረስ በየእልፍ እልፍ እየሰገደ ኖረ።
ከዚያም የትግራይን አውራጃዎች ሁሉ ዞረ፤ ወደ ሰሜንም ምድር ተሻግሮ ከያሬድ መቃብር ገባ በደጃፉም ላይ ተቀርጾ አግኝቶ አንቀጸ ብርሃንን ተማረ፤ ሲመለስም ሽፍቶች አግኝተውት በደንጊያ ወገሩት በበትርም ደበደቡት በጦርም ወግተው ጥለውት ሔዱ፤ አምላክን የወለደች እመቤታችንም ቅድስት ድንግል ማርያም ወደርሱ መጥታ አዳነችው፤ አንዲት ቀንም የሴት በድን አግኝቶ በላይዋ ባማተበ ጊዜ ተነሣች፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ሦስት ጊዜ ሒዶ ከከበሩ ቦታዎች ተባርኳል ወደ አባቶቻችን ሐዋርያት መቃብርም እስከ ሀገረ ባርቶስና ሕንደኬ ደረሰ፤ ውኃው ከመላበት ወንዝም በሚደርስ ጊዜ በላዩ አማትቦ እንደ የብስ በእግሩ እየረገጠ ይሻገረዋል።
አንበሶችና ነብሮች ይከተሉታል ምግብ በአጡ ጊዜ ደንጊያውን ባርኮ ሥጋ አድርጎ ይሰጣቸዋል፤ ከዚህ በኋላም ወደ አባታችን ተክለሃይማኖት ገዳም ደብረ ሊባኖስ ሔደ፤ ከአባ ተወልደ መድኅንም እጅ አስኬማ ተቀበለ አባ ተወልደ መድኅንም ሊፈትነው ወዶ ሰባት የጽድ ቅርንጫፍ ሰብሮ ትከለው ብሎ ሰጠው በተከላቸውም ጊዜ ወዲያውኑ በቅለው አደጉ እስከ ዛሬም አሉ።
ብዙዎችም ወደርሱ መጥተው በእርሱ እጅ መነኰሱ በእግዚአብሔር አብና አምላክን በወለደች በእመቤታችን ድንግል ማርያም ስም በአነፃቸው አብያተ ክርስቲያን በአንድነት ኖሩ፤ በአንዲት ዕለትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕጣንን ሰጠችውና ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋራ የአሸናፊ እግዚአብሔርን መንበር አጠነ፤ ብዙ ጊዜም ወደርሱ ሐዋርያት እየመጡ ይባርኩታል፤ በአንዲት ዕለትም ነብር ከእናቱ እጅ ሕፃንን ነጥቆ ወሰደ በአባ ዮሴፍም ስም በአማጸነችው ጊዜ በሦስተኛው ቀን መለሰላት፤ ለልጆቹም ገንዘብም ሆነ የእንስሳ ጥሪት እንዳያደርጉ ሥጋ እንዳይበሉ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ ትሕትናን ቅንነትን እንዲማሩ ከንቱ ነገር ቧልትን እንዳይናገሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳይስቁ ይህ ሁሉና የመሳሰለውን ሥርዓትን ሠራላቸው፤ ከዚህ በኋላም ሩጫውን በፈጸመ ጊዜ በሰላም በፍቅር አረፈ ደብረ ታቦር ብሎ በሰየማት ቤተ ክርስቲያንም ተቀበረ ከእርሱም ቁጥር የሌላቸው ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የቅዱሳኑ በረከት ይደርብን።
(ስንክሳር ዘወር ግንቦት 19)
🗓 የግንቦት 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አባ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ (ኢትዮዽያዊ)
2.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም (የ12ቱ ሐዋርያት መቃብር
ከጌታ የተገለጠላቸው ኢትዮዽያዊ)
3.አቡነ ብስጣውሮስ ዘሐይቅ እስጢፋኖስ (ኢትዮዽያዊ)
4.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት ታላቁ (7 ጊዜ ሙቶ የተነሳ)
5."805,007" ሰማዕታት (በአንድ ቀን ብቻ የተገደሉ)
6.አባ ይስሐቅ ገዳማዊ
🗓ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ
4. አባ ስነ ኢየሱስ ጻድቅ
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በፃድቃንና ሰማዕታት አማላጅነት ይማረን አሜን።
25/05/2026
፲፰
ስም
ግንቦት ዐሥራ ስምንት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ከዐረገ በኋላ በዐሥረኛ ከትንሣኤው በሃምሳኛ ቀን ለደቀመዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን የላከበት ነው፣ የአባ አብርሃም ጓደኛ የከበረ አረፈ፣ መታሰቢያው ነው በረከቱ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
(በዓለ_ጰራቅሊጦስ)
ግንቦት ዐሥራ ስምንት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ከዐረገ በኋላ በዐሥረኛ ከትንሣኤው በሃምሳኛ ቀን ለደቀመዛሙርቱ ከአብ የሚሠረጽ ሌላ አካላዊ ሕይወት ጰራቅሊጦስን እልክላችኋለሁ ብሎ ተስፋ እንደ ሰጣቸው በሐዋርያት ላይ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።
እናንተም ከአርያም ኃይልን እስከምትለብሱ በኢየሩሳሌም ኑሩ አላቸው። ሁለተኛም ያ እውነተኛ መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ ዕውነት ሁሉ ይመራችኋል አላቸው። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው እርሱም አለቃቸው የሆነ ጌታችን አጽናኚውን ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ነው ሊልክልን ተስፋ አስደርጎናል የምናሰማውንና የምናደርገውን ልብ ያስደርገን ዘንድ።
ይህንንም ሲነግራቸው እነሆ የዐውሎ ነፋስ ድምፅ ሰሙ በዓለም ውስጥ እንደርሱ ያለ የማያውቁት ጣፋጭ መዓዛ አሸተቱ። የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎችም በየአንዳንዳቸው ላይ ሲወርዱ ታዩ። በአዲስ ቋንቋም ተናገሩ ለጌትነቱ እጅ መንሻ ሊሆን አርባ ቀን ጾሙ። ሁለተኛም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በዓለ ኃምሣ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሁነው አብረው ሳሉ። ድንገት ከሰማይ የዐውሎ ነፋስ ድምፅ መጣ ተቀምጠው የነበሩበትም ቤት ሁሉ መላው።
የተከፋፈሉ የእሳት ልሳኖችም ታዩአቸው በየአንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው ሁሉም መንፈስ ቅዱስን ተመሉ። በየራሳቸውም በሀገሩ ሁሉ ቋንቋ ይናገሩ ጀምር መንፈስ ቅዱስ ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው። ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር።
ይህንንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ደንግጠው ሁሉም ተሰበሰቡ በየሀገራቸው ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተዋቸዋልና።ተደንቀውም በድንጋጤ እንዲህ አሉ። እነሆ እሊህ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን የጳርቴና የሜድ የኤላሜጤም ሰዎች ስንሆን። በሁለት ወንዝም መካከል በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም በፍርግያም በጵንፍልያም በግብጽም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊብያ ወረዳዎች የምንኖር በሮሜም የምንቀመጥ አይሁድም ወደ ይሁዲነት የገባን የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ስንሆን የእግዚአብሔርን ገናናነት በቋንቋችን ሲናገሩ እነሆ እንሰማቸዋለን።
ሁሉም ደንግጠው የሚናገሩትን አጡ። እርስ በርሳቸውም እንጃ ይህ ምን ይሆን አሉ ሌሎች ግን እያፌዙባቸው ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ። ጴጥሮስም ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ ቆመ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው። የይሁዳ ሰዎች በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን ቃሎቼንም አድምጡ።
ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና። ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው እግዚአብሔር አለ በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አሳድራለሁ። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢትን ይናገራሉ ጐበዛዝቶቻችሁም ራእይን ያያሉ ሽማግሎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ።
ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ መንፈስ ቅዱስን አሳድራለሁ ትንቢትን ይናገራሉ። ድንቆችን በላይ በሰማይ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ። ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል ታላቅ የሆነ የጌታ ቀንም ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል።የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።
ዳዊትም እንዲህ አለ ቅዱስ መንፈስህን ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ ደስ የሚያሰኝ ደኅነትህንም ስጠኝ። በጽኑዕ መንፈስህም አጽናኝ ለዝንጉዎች ሕግህን እንዳስተምራቸው። ሁለተኛም መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉ አለ። ደግሞ ቅዱስ መንፈስህ በጽድቅ ምድር ይምራኝ አለ።
ደግሞም በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ ሠራዊቶቻቸው ሁሉ በአፉ እስትንፋስ። ኢሳይያስም እንዲህ አለ በእኔ ህልውና ያለ ያዋሐደኝ ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስ ለድኆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ ለተማረኩትም ነፃነትን የእግዚአብሔርንም ዓመት የተመረጠ እለው ዘንድ ላከኝ። ጌታችንም እንዲህ አለ ከእናንተ ጋራ ሳለሁ ይህን ነገርኳችሁ። ነገር ግን አብ በስሜ የሚልከው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። እኔ ሰላምን እተውላችኋለሁ የአባቴንም ሰላም እሰጣችኋለሁ። እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው ስጦታ አይደለም።ልባችሁ አይታወክ አትፍሩም ።
እኔ እሔዳለሁ ወደእናንተም ተመልሼ እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። ሁለተኛ ደግሞ እንዲህ አለ እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚገኝ የዕውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለእኔ ይመሰክራል። እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋራ ኖራችኋልና ምስክሮቼ ናችሁ።
እንዳትሰነካከሉ ይህን ነግሬአችኋለሁ ከምኵራባቸው ያወጡአችኋል ከዚህም በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንደሚያቀርብ የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። እኔም ዕውነት እነግራችኋለሁ እኔ ብሔድ ይሻላችኋል እኔ ካልሔድኩ ግን አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ወደ እናንተ አይመጣምና። ከሔድኩ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ ።
እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይውቅሰዋል። ስለ ኃጢአት በእኔ አላመኑምና ስለ ጽድቅም ወደ አብ እሔዳለሁና እንግዲህም አታዩኝምና ስለ ፍርድም የዚህ ዓለም ገዢ ይፈረድበታልና አላቸው።
የምነግራችሁም ገና ብዙ አለኝ ነገር ግን ዛሬ ልትሸከሙት አትችሉም እርሱ የዕውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና የሚመጣውንም ይነግራችኋል።
እርሱ እኔን ይገልጣል ከእኔም ገንዘብ አድርጎ ይነግራችኋልና ለአባቴ ያለው ሁሉ የኔ ገንዘብ ነውና ስለዚህ ከእኔ ገንዘብ አድርጎ ይነግራችኋል አልኳችሁ። ጥቂት ጊዜ አለ አታዩኝም ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ ታዩኛላችሁ ወደ አብ እሔዳለሁና ።
ደቀ መዛሙርቱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ ምንድነው ይህ ነገር ጥቂት ጊዜ አለ አታዩኝም ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ ታዩኛላችሁ ወደ አብ እሔዳለሁና የሚለን። ጌታ ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደሚሹ ዐወቀባቸው እንዲህም አላቸው ስለዚህ ነገር እርስ በርሳችሁ ትመራመራላችሁን ጥቂት ጊዜ አለ አታዩኝም ደግሞም ጥቂት ጊዜ አለ ታዩኛላችሁ ስለአልኳችሁ።
እውነት እውነት እላችኋለሁ እናንተ እንደምታዝኑ እንደምታለቅሱ ዓለም ደስ ይለዋል እናንተ ግን ታዝናላችሁ ነገር ግን ኀዘናችሁ ደስታ ይሆናችኋል። ሰው የሆነበትንም ሥራ በፈጸመ ጊዜ ሒዱና አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ። ስታጠምቋቸውም በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ በሉ። ያዘዝኳችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሩአቸው እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ አላቸው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት የአባ አብርሃም ጓደኛ የከበረ አባ ገዐርጊ አረፈ። ይህም ቅዱስ የክርስቲያን ወገን ነው ወላጆቹ ደጎች ጻድቃን ናቸው። በአደገም ጊዜ የወላጆቹን ከብቶች የሚጠብቅ እረኛ ሆነ። ሁል ጊዜም የምንኵስና ልብስ ይለብስ ዘንድ በልቡ ይመኝ ነበር።
ዐሥራ አራት ዓመትም በሆነው ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ አነሣሳችው በጎቹንም ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ። እየተጓዘም ሳለ ከሩቅ የብርሃን ምሰሶ አየ ወደ ወንዝ እስከ ደረሰ ድረስ ወደ ርሱ ሔደ ከዚህም በኋላ ያ የብርሃን ምሰሶ ከእርሱ ተሰወረ።
ያንንም ወንዝ በተሻገረ ጊዜ በሽማግሌ አምሳል ሰይጣን ተገለጠለትና ልጄ ሆይ ዕወቅ ስለ አንተ ልብሱን ቀዶ አባትህን አየሁት እርሱም ያዝናል ያለቅሳል ተመልሰህ የአባትህን ልብ ልትአጽናና ይገባሃል። የዱር አውሬ ነጥቆ የበላህ መስሎታልና አለው።
አባ ገዐርጊም ደንግጦ አንድ ሰዓት ያህል ቆመ ከዚህም በኋላ የከበረ ወንጌል ከእኔ ይልቅ አባቱንና እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም ደቀ መዝሙሬም ሊሆን አይችልም ብሏል ብሎ አሰበ።
ይህንንም በአለ ጊዜ ሰይጣን እንደ ጢስ ሆኖ ተበተነ።አባ ገዐርጊም ሰይጣን እንደ ሆነ አወቀ በዚያን ጊዜም ያ የብርሃን ምሰሶ ደግሞ ተገለጠለት የእግዚአብሔርም መልአክ በመነኵሴ አምሳል አብሮት ተጓዘ ቅዱሱም መልአኩን ተከተለው እርሱም ከአባ አርዮን ገዳም አደረሰው። አባ ገዐርጊም ከአንድ ጻድቅ ሰው መነኵሴ ጋራ በዚያ ዐሥራ አራት ዓመት ወጥ ሳይቀምስ ወይን ሳይጠጣ የአትክልት ፍሬም ቢሆን በዚህ በዐሥራ አራት ዓመት ያህል ከሚቀመጥ በቀር አልተኛም።
ተጋድሎውንም በጨመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና እንዲህ አለው ሥጋህ እንዳይደክም በመካከለኛ ገድል ተጋደል ብሎሃል ጌታ። ከዚህም በኋላ ሊሠራው የሚገባውን ሥርዓት ሠራለት። ሁል ጊዜም እስከሚመሽ እንዲጾም ትንሽም እንጀራን እንዲበላ ከአራት ሰዓት እስከ መንፈቀ ሌሊት ስለ ሥጋው ዕረፍት እንዲተኛ በቀረው ሌሊት እስቲነጋ ተግቶ እንዲጸልይ።
በዚህም ተጋድሎ ብዙ ዘመናት እየተጋደለ በኖረ ጊዜ በበረሀ ውስጥ ብቻውን ሊኖር ወዶ በጫካ ውስጥ እየተመላለሰ ሁለት ዓመት ኖረ። ከዚህም በኋላ ጌታ ተገልጾለት ወደ ቦታው እንዲመለስ አዘዘው። ያን ጊዜም አምላካዊት ኃይል ከከበሩ መክሲሞስና ደማቴዎስ ገዳም አደረሰችው እርሷም ለደብሩ አቅራቢያ ናት።
ወደ ደብሩም በተመለሰ ጊዜ በዚያን ወቅት አብርሃም ከዓለም ወደዚያ ገዳም መጥቶ ሁለቱም ተገናኙና በአንድነት ተስማምተው የአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ወደ ሆነ ወደ አባ ዮሐንስ ደረሱ። እርሱም ቦታ ሰጥቷቸው በውስጡ ኖሩ ያ ቦታም እስከ ዛሬ ታውቆ ይኖራል ።
ያቺም ዋሻ በግቢግ ትባላለች የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐለት የሆነ ጣሪያዋን ሠንጥቆ ወደ እነርሱ የወረዳበት ናት። እነርሱም ሰገዱለት ሰላምታም ሰጥቷቸው አጽናንቷቸው ከእርሳቸው ዘንድ ዐረገ።በዚያችም ጌታችን በወረደበት መስኮት ብርሃንን አዩ እስከ ዛሬም የተከፈተች ሁና ትኖራለች።
እሊህ ቅድሳንም ለመነኰሳት የሚሆን ብዙ ድርሳናትንና ብዙ ተግሣጻትን ደረሱ። ለአባቶቹ የሚታዘዘውንና የሚገዛውን አመሰገኑት። ከዚህም በኋላ አባ አብርሃም ጥር ሁለት ቀን አረፈ።ከእርሱ በኋላም የከበረ አባ ገዐርጊ በዚች በግንቦት ወር በዐሥራ ስምንት ቀን አረፈ። መላ ዕድሜውም ሰባ ሁለት ዓመት ሆነ።በዓለም ዐሥራ አራት ዓመት በምንኩስና ኃምሳ ስምንት ዓመት ነው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ዕለት የሰማዕት ሲኖዳ መታሰቢያው ነው በረከቱ፡ ሰማዕቱ አቡነ ሲኖዳ ሀገራቸው ግብፅ ብሕንሳ ነው፡፡ መጽሐፍ ሰማዕትም ጻድቅም ይላቸዋል፡፡ ሽኖዳ እየተባሉም የሚጠሩ ሲሆን የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የአክስት ልጅ ናቸው፡፡ ሙሉ ዕድሜያቸውን በገዳም ነው የኖሩት፡፡ በማርቆስ መንበር ላይ ተሹመው በፓትርያርክነት እያገለገሉ እያለ በዘመናቸው ከሃዲው ንጉሥ መክስምያኖስ ነግሦ ስለነበር ክርስቶስን በማመናቸው እጅግ ብዙ አሠቃይቷቸዋል፡፡
ከሃዲው ንጉሥ መክስምያኖስ ወደ እርሱ እንዲመጡ ካደረገ በኋላ በእርሱ ጣዖት እንዲያምኑ ጠየቃቸው፡፡ አቡነ ሲኖዳም በክርስቶስ እንደሚያምኑ ሲነግሩት በምድር ላይ ደማቸው እንደ ውኃ እስኪፈስ ድረስ ጽኑ ግርፋትን አስገረፋቸው፣ ዐይናቸውም ሊወጣ ደረሰ፡፡ በእሥር ቤትም ከጣሏቸው በኋላ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ከቁስላቸው ፈውሶ አበረታቸውና ገና እንደሚጋደሉ ነገራቸው፡፡ ንጉሡም ‹‹ሞቶ እንደሆን እዩት›› ብሎ ወታደሮቹን ቢልክም ፍጹም ጤነኛ መሆናቸውን ነገሩት፡፡ ልብሳቸውንም አስወልቆ አይቶ ካረጋገጠ በኋላ ‹‹ታላቅ ሥራይ ነው›› በማለት ዘቅዝቀው እንዲሰቅሏቸውና ከሥር እሳት እንዲያነዱባቸው አዘዘ፡፡ ይህንንም በአባታችን ላይ አደረጉባቸው፡፡ አሁንም ምንም ዓይነት ሥቃይ እንዳልገደላቸው ባየ ጊዜ በብዙ ካሠቃያቸው በኋላ መጋቢት 14 ቀን አንገታቸውን በሰይፍ አስቆርጦታል፡፡
=>ግንቦት 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን ሐዋርያት ወአርድእት
2.አባ ገዐርጊ ገዳማዊ
3.ቅዱስ ሲኖዳ ሰማዕት
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ
ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከቸር አባቱ አዳኝና ሕይወት ከሆነ ቅዱስ መንፈሱ ጋር ጌትነት ክብር ምስጋና ይሁን። እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
( እና )
24/05/2026
፲፯
ስም
ግንቦት ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን የከበረ አባት ታላቅና የተመሰገነ የቆጵሮስ ኤጲስቆጶስ አረፈ፣ የኢትዮጵያዊው ጻድቅ ገርዓልታና ሐውዜን ላይ እጅግ አስገራሚ ታላላቅ ገዳማትን የገደሙት ዕረፍታቸው ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ግንቦት ዐሥራ ሰባት በዚች ቀን የከበረ አባት ታላቅና የተመሰገነ የቆጵሮስ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ አረፈ።
ይህም ቅዱስ ከቤተ ገብርኤል ዐፀድ አቅራቢያ ነው ወላጆቹም በኦሪት ሕግ የጸኑ አይሁድ ናቸው። እነርሱም ድኆች ናቸው አባቱም ገባር ስለ ነበረ ይህን ቅዱስና አንዲት እኅቱን ሳያሳድጋቸው ሞተ እርሱም አንድ ክፉ አህያ ነበረውና የተወላቸው እርሱን ነው እናታቸውም የኦሪትን ትምህርት በማስተማር አሳደገቻቸው።
እናቱም አህያውን እንዲሸጠውና ከእርሱም እንዲያርፍ በሺያጩም እንዲረዳ ኤጲፋንዮስን መከረችው። ሊሸጠውም ከአህያው ጋራ ሲጓዝ አንድ ክርስቲያን ጻድቅ ሰው ስሙ ፊላታዎስ የሚባል ተገናኘው ያንን አህያ ሊገዛ ወዶ ከኤጲፋንዮስ ጋራ ቁሞ ሲነጋገር ያን ጊዜ አህያው ኤጲፋንዮስን ኵላሊቱን ረገጠው በምድር ላይ ወድቆ ለመሞት ደረሰ። አባ ፊላታዎስም በመስቀል ምልክት ኵላሊቱ ላይ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሎ አማተበ ቅዱስ ኤጲፋንዮስም ያን ጊዜ ከሕማሙ ድኖ ተነሣ ከቶ ምንም ሕማም እንዳልነካው ሆነ። ከዚህ በኋላም አባ ፊላታዎስ በዚያ ክፉ አህያ ላይ እንዲህ ብሎ ጮኸ ስለ እኛ በተሰቀለው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ትሞት ዘንድ ይገባል ወዲያውኑ ያ አህያ ወድቆ ሞተ።
ቅዱስ ኤጲፋንዮስም እሊህን ሁለት ተአምራት አይቶ በስሙ ተአምራት የምታደርግበት የተሰቀለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማነው ብሎ አባ ፊላታዎስን ጠየቀው። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት የክብር ባለቤት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም አይሁድ የሰቀሉት ነው አለው ይህም ነገር በቅዱስ ኤጲፋንዮስ ልብ ተቀረጸ።
በዚያም ወራት አንድ ባለጠጋ አይሁዳዊ ነበር ኤጲፋንዮስንም ወሰደው የኦሪትንም ሕግ በማስተማር አሳደገው። የሚሞትበትም በቀረበ ጊዜ ልጅ ስለሌለው ጥሪቱን ሁሉ አወረሰው የኦሪትንም ሕግ ትምህርት ሁሉ ተማረ።
በአንዲት ዕለትም ስሙ ሉክያኖስ ከሚባል መነኰስ ጋራ ተገናኘ እርሱም የተማረና የእግዚአብሔር ጸጋ ያደረበት ነው ከእርሱ ጋር ተጓዘ። ሁለቱም በአንድነት ሲጓዙ ድኃ ሰው አገኛቸውና ምጽዋትን እንዲሰጠው ያንን መነኰስ ለመነው። ገንዘብም ስለሌለው የሚለብሰውን የጸጉር ዐጽፍ አውልቆ ለድኃው ሰጠው በዚያን ጊዜ ለዚያ መነኰስ የብርሃን ልብስ ከሰማይ ሲወርድለት ኤጲፋንዮስ አየ።
ስለዚህም ድንቅ ተአምር አደነቀ ከመነኰስ እግር በታች ሰግዶ አንተ ማነህ ሃይማኖትህስ ምንድ ነው ብሎ ጠየቀው እርሱም ክርስቲያን እንደሆነ ነገረው። ደግሞ ክርስቲያን እንዲያደርገው ለመነው መነኵሴውም ኤጲፋንዮስን ወስዶ ወደ አንድ ኤጲስቆጶስ አደረሰው። እርሱም የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሥርዓቷንም ሁሉ አስተማረው።
ኤጲፋንዮስም ኤጲስቆጶሱን እኔ መነኰስ መሆን እፈልጋለሁ አለው ኤጲስቆጶሱም ብዙ ገንዘብ እያለህ መነኰስ መሆን አይገባም አለው።
ኤጲፋንዮስም ሒዶ እኅቱን አምጥቶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃት ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች ለባልቴቶችና ለሙት ልጆች ለአብያተ ክርስቲያናትም ሰጠ መጻሕፍትንም ከእርሱ ገዛ።
ከዚህ በኋላ መነኰሰ ለእርሱም ለእኅቱም ለጥምቀት ምክንያት ወደሆነው ስሙ ሉክያኖስ ወደተባለው መነኰስ ገዳም ገባ ዕድሜውም ዐሥራ ስድስት ዓመታት ነበረ።
ከዚህም በኋላ ታላቁን አባ ኢላርዮስን አገኘው እርሱም በዕድሜው ጐልማሳ በገድልም ሽማግሌ ነው። ቅዱስ ኤጲፋንዮስንም ተቀብሎ የምንኵስናን ሕግና የክርስትናን ሥርዓት አስተማረው የእግዚአብሔርም ጸጋ አድሮበት የቤተ ክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት የምንኵስናንም ሕግ በጥቂት ቀኖች አጠና።
ከዚህ በኋላ ታላላቅ ተአምራቶችን በመሥራት ሙታንን እስከሚአስነሣቸው ሰይጣናትን ከሰዎች ላይ እስከሚያስወጣቸው ውኃ ከሌለበት ከደረቅ ቦታ ውኃን እስከሚአፈልቅ ያለ ጊዜውም ብዙ ዝናምን እስከ ማውረድ ደርሶ በገድልና በትሩፋት ፍጹም ሆነ።
የትሩፋቱም ወሬ አዋቂነቱም ተሰማ ከእርሱ ጋራም ሊከራከሩ ብዙ አይሁድ ወደ እርሱ መጡ። ስሕተታቸውንም ገለጠላቸው በእርሱ ትምህርት አምነው የክርስትናን ጥምቀት አጠመቃቸው። እንዲሁም ጥበበኞች ዮናናውያን በትምህርቱ ተመለሱ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖትም ውስጥ ገቡ።
መምህሩ ቅዱስ ኢላርዮስም በቆጵሮስ ሀገር ኤጲስቆጶስነት እንደሚሾም ትንቢት ተናገረለት። ወደዚያም ሒዶ በታዘዘለት ቦታ በዚያ እንዲኖር አዘዘው። እንዲህም አለው ኤጲስቆጶስነት ሊሾሙህ በፈለጉህ ጊዜ እምቢ አትበል ይህ በእግዚአብሔር ፍቃድ ሆኖአልና።
ቅዱስ ኤጲፋንዮስም ወደ ቆጵሮስ ሒዶ መምህሩ ቅዱስ ኢላርዮስ በአዘዘው ቦታ ተቀመጠ።
የቆጵሮስ ደሴት ኤጲስቆጶስም በአረፈ ጊዜ በዚያን ሰሞን ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ምግቡን ሊገዛ ወደ ገበያ ገባ። ከእርሱም ጋራ ሁለት መነኰሳት አሉ። ደግሞም በዚያች ገዳም ጻድቅ የሆነ ሽማግሌ ኤጲስቆጶስ ነበረ ለእርሱም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ነገረው። ወደ ገበያም ሒድ በእጁም ሁለት የወይን ዘለላ የያዘ መነኰስ ታገኛለህ ከእርሱ ጋራም ሁለት መነኰሳት አሉ ስሙንም ጠይቀው። ስሜ ኤጲፋንዮስ ነው ይልሃል እርሱን ያዝ በእጁ ያለውንም አስጥለህ ከአንተ ጋራ አምጣው።
ያ ኤጲስቆጶስም የክበር ባለቤት ጌታችን እንደ አዘዘው አደረገ በአመለከተውም ቦታ አግኝቶት ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስዶ ዲቁና ሾመው። በሦስተኛውም ቀን ኤጲስቆጶስነት ሾሙት። ከዚህም በኋላ ሽማግሌው ኤጲስቆጶስ የኤጲፋንዮስን ልብ ደስ ለማሰኘት ሽቶ ስለ ኤጲፋንዮስ ያየውን ራእይ ለሕዝቡ ገለጠላቸው። ስለ ርሱም ታላቅ ደስታ ሆነላቸው።
ይህም ቅዱስ እግዚአብሔር በሚወድለት በሹመቱ ሁኖ በበጎ ሥራ ላይ ጸና። ጥቅም ያላቸውን ብዙ ድርሳኖችንም ደረሰ። ርኅራኄ ስለ ሌለው ሰው በሚሰማ ጊዜ ተመልሶ ቸር እስከሚሆን ድረስ ሁልጊዜ ይገሥጸዋል ይመክረዋል።
በኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ በአባ ዮሐንስ ላይ ምክንያት ፈጠረ ስለ ርሱ ርኅራኄ እንደሌለው በሰማ ጊዜ ከወርቅ የተሠሩ የማዕዱን ዕቃዎች የሚመገብባቸውን በውሰት ወሰደ። እነርሱም ወርቅና ብር ናቸው ቅዱስ ኤጲፋንዮስም ሸጣቸውና ለድኆችና ለምስኪኖችም መጸወታቸው።
አባ ዮሐንስም እንዲመልስለት በሻ ጊዜ ምንም ምን አልሰጠውም። በክብር ባለቤት ጌታ መቃብር ቤተክርስቲያን ውስጥ ቅዱስ ኤጲፋንዮስን የልብሱን ጫፍ ስጠኝ ብሎ ያዘው። ቅድስ ኤጲፋንዮስም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ የአባ ዮሐንስም ዐይኖቹ ያንጊዜ ታወሩ። ከዚህ በኋላም ይምረው ዘንድ በብዙ ልቅሶ ወደርሱ ፈጽሞ ማለደ ዐይኖቹንም ይገልጥለት ዘንድ ለመነው።
ሁለተኛም ቅድስ ኢጲፋንዮስ ጸለየ አንድ ዐይኑንም ገለጠለት የማዕዱንም ዕቃዎች ሸጦ ለድኆችና ለምስኪኖች እንደሰጣቸው ነገረው። ስለ ዮሐንስ አፈወርቅ መሻርና መሰደድ ወደርሷ መጥቶ ይራዳት ዘንድ አውዶክስያ ንግሥት ጽፋ ወደርሱ በላከች ጊዜ ሊአስታርቃቸውና በመካከላቸው ሰላምን ሊአደርግ ሽቶ ወደ ቊስጥንጥንያ ሔደ። ነገር ግን ቅዱስ ኤጲፋንዮስን አልሰማችውም ዮሐንስን ከሹመቱ ካልሻርከው ይህ ካልሆነ አብያተ ክርስቲያናትን እዘጋለሁ የጣዖታትንም ቤቶች እከፍታለሁ አለችው።
ቅዱስ ኤጲፋንዮስም ፈጽሞ እያዘነ ከእርሷ ዘንድ ወጣ። ምን እንደሚአደርግም ያስብና ይጨነቅ ነበር።የንግሥት ባሮቿ ግን እነሆ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ዮሐንስ አፈወርቅን ከሹመቱ ሻረው እያሉ በቊስጥንጥንያ ከተማ በሐሰት አወሩ።
ቅዱስ ዮሐንስም ይህን ወሬ በሰማ ጊዜ ወደ ኤጲፋንዮስ እንዲህ ሲል ላከ። ለምን ያለ ፍርድ በእኔ ላይ ይህን አደረግህ አንተ ወደ መንበረ ሢመትህ እንደማትደርስ ዕወቅ። ኤጲፋንዮስም ለመልእክቱ መልስ እንዲህ ሲል ጻፈ። ስለ አንተ ምንም ምን የጻፍኩትና ከንግሥት ጋራ የተስማማሁት ነገር የለም አንተም ከስደት እንደማትመለስ ዕወቅ።
ከዚህ በኋላም ወደ መንበረ ሢመቱ ሊሔድ ሽቶ ከቊስጥንጥንያ ወጥቶ በመርከብ ተሳፈረ እግዚአብሔርም የዮሐንስን ጽድቅ ሊገልጽ ከመንበረ ሢመቱ ሳይደርስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በመርከብ ውስጥ አረፈ። እንዲሁም የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ክብር እንዲገለጥ ቅዱስ ዮሐንስ በተሰደደበት አረፈ።
የከበረ ኤጲፋንዮስም የሚያርፍበትን ጊዜ አውቆ ተነሥቶ ጸለየ። ለደቀ መዛሙርቱም እነርሱ ኤጲስቆጶሳት እንዲሆኑ ነገራቸው በሰላምታም ተሰናብቷቸው ከዚህ በኋላ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን የኢትዮጵያዊው ጻድቅ ገርዓልታና ሐውዜን ላይ እጅግ አስገራሚ ታላላቅ ገዳማትን የገደሙት የአቡነ ገብረ ሚካኤል ዕረፍታቸው ነው፡፡ እኚህ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ በታላቅ ተጋድሎአቸው ይታወቃሉ፡፡ የትውልድ ሀገራቸው ትግራይ ገርዓልታ ነው፡፡ ጻድቁ አቡነ ገብረ ሚካኤል ወንጌልን ዞረው በማስተማርና አስደናቂ ፍልፍል ዋሻ ቤተ መቅደሶችን በማነጽ ብዙ የደከሙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ እጅግ አስናቂው ገዳማቸው ገርዓልታ ጠራሮ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል፡፡
ከገርዓልታ በደቡባዊ አቅጣጫ የሚገኘው ይህ የአቡነ ገብረ ሚካኤል አስደናቂ ገዳም እንደ ደብረ ዳሞ በገመድ ብቻ ከሚወጣው ከአቡነ ገብረ ናዝራዊ ገዳም ጋር የሚዋሰን ሲሆን ገዳሙ ለመድረስ የመኪናውን መንገድ ከጨረሱ በኋላ በእግር አንድ ሰዓት ይፈጃል፡፡
በገዳሙ ውስጥ ጻድቁ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ብዙ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ የጌታችን የሾህ አክሊል ምሳሌ የሆነውና ጻድቁ ያደርጉት የነበረው የድንጋይ ቆብ፣ መቋሚያቸው፣ የእጅ መስቀላቸውና መጻሕፍቶቻቸው ይገኛሉ፡፡ ሌላው አስደናቂ ነገር ሀገሩ በረሃ ቢሆንም ጻድቁ ከኢየሩሳሌም ዮርዳኖስ ያመጡትና ዋሻው ውስጥ ጉድጓድ ቆፍረው ያጠራቀሙትን ውኃ መነኮሳቱ ሁልጊዜ የሚጠቀሙበት ቢሆንም ውኃው ግን ከዓመት እስከ ዓመት መጠኑ አይቀንስም፡፡ ሊቀ ብርሃናት መርቆርዎስ አረጋ የቅዱሳን ታሪክና ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን በሚሉት ሁለት መጽሐፎቻቸው ላይ እንደጠቀሱት በገዳሙ ውስጥ ከዓመት እስከ ዓመት የምትበራው አንዲት ጧፍ ብቻ ናት፡፡ ጧፏ ነዳ የማታልቅ ስትሆን አለቀች ትቀየር ሳትባል አስገራሚ በሆነ ተአምር ከዓመት እስከ ዓመት ትበራለች፡፡
ሌላኛው የአቡነ ገብረ ሚካኤል አስደናቂ ፍልፍል ዋሻ ቤተ መቅደስ ከሀውዜን ከተማ በስተደቡብ አቅጣጫ ከአስደናቂው የአቡነ ይምዓታ ጎሕ ገዳም 16 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ነው፡፡ ጠራሮ ቀበሌ ውስጥ የሚገኘው ይሄኛውም ገዳማቸው በተፈጥሮአዊ አቀማመጡ አስደናቂ ነው፡፡ አቡነ ገብረ ሚካኤል አስደናቂውን ዋሻ ፈልፍለው ከጨረሱ በኋላ ግድግዳውና ዓምዶቹ ላይ የሳሏቸው የሐዋርያትና የቅዱሳን ሥዕላት ከጥንታዊነታቸው በተጨማሪ እጅግ ውብና አስደናቂ ናቸው፡፡ ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ ጻድቁ ቅዱሳት ሥዕላቱን የሳሏቸው በሸራ ላይ ሳይሆን በአሸዋማው የዋሻው ፍልፍል ግድግዳ ላይ መሆኑ ነው፡፡
🗓 ግንቦት 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1. ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)
2. ቅዱስ ኢላርዮን ገዳማዊ
3. አባ ሉክያኖስ ጻድቅ
4. ቅዱስ ፊላታዎስ ክርስቲያናዊ
🗓 ወርኀዊ በዓላት
1. ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3. ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4. አባ ገሪማ ዘመደራ
5. አባ ዸላሞን ፈላሢ
6. አባ ለትጹን የዋህ
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
( እና )
23/05/2026
፲፮ †
አንድ አምላክ በሆነ ስም
ግንቦት ዐሥራ ስደስት በዚችም ቀን
መታሰቢያው ነው፣ ዕውቀትን ከልቡ ያፈለቀ የኢየሩሳሌሙ ሰው አረፈ፣ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ከዚህ ዓለም ከሞት ተሰወሩ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
( )
ግንቦት ዐሥራ ስደስት በዚችም ቀን የወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ መታሰቢያው ነው። በእስያና በኤፌሶን በዙሪያቸው በአሉ አገሮች ሁሉ ስለ መስበኩና ከባሕር በመስጠምም ወደ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር እስከ መለሳቸውና የክብር ባለቤት ጌታችን በእጆቹ ላይ የሚያደርገው ተአምራት በትምህርቶቹም ከሰይጣን ወጥመድ እስከ አዳናቸው ድረስ ጣዖታትን ከሚያመልኩ ከክፉዎች ሰዎች ስለደረሰበት መከራ ነው።
በሸመገለም ጊዜ ወንጌልን ጻፈላቸው ሦስቱ ወንጌላውያን ያስቀሩትን እስከሚጽፍ መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቶታልና የወልድንም አኗኗሩንና ሰው መሆኑን ዓለም የማይወስነውንም ተአምራቱን። ከዚህ በኋላም ወደ ሰማይ እንደ ወጣና በሰማይ የሚኖሩ የመላእክት ሠራዊት ሥርዓታቸውን አይቶ አቡቀለምሲስ የሚባለውን ጻፈ።
ለስብከቱም የበዓሉ መታሰቢያ ሊሆን ግብጻውያን ይህን ሠሩ ዳግመኛም በእስክንድርያ አገር ውስጥ ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ቀን ነው። (ስንክሳር ዘወርኀ ግንቦት 16)
ተጨማሪ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ለመስበክ ዕጣ የደረሰው እስያ ስለነበር ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን አስከትሎ ሄደ፡፡ ይኽችውም ኤፌሶን በጥንቱ በታናሽ እስያ በዛሬው የቱርክ ግዛት ውስጥ ከተማ ናት፡፡ ዛሬ ኢያዞሎክ ተብላ የጥንት ታሪኳ ጠፍቷል፡፡ አስቀድሞ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ሰብኮባታል፡፡ ደቀ መዝሙሩን ቅዱስ ጢሞቴዎስንም በከተማዋ ላይ ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ እርሱም በግፍ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ቅዱስ ዮሐንስን እየረዳው በከተማዋ ብዙ አገልግሏል፡፡ በኋላ ግን በግፍ ገድለውታል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ኤፌሶን ለመሄድ በመርከብ ሲሳፈር መርከቡ በማዕበል ተሰበረ፡፡ ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን መዕበሉ ወደ አንዲት ደሴት አደረሰው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በመርከቡ ስባሪ ተንጠልጥሎ በባሕሩ ማዕበል መካከል 40 ቀንና 40 ሌሊት ከኖረ በኋላ ማዕበሉ ተፍቶ አብሮኮሮስ ካለበት ደሴት አደረሰውና ተያይዘው ኤፌሶን ከተማ ገቡ፡፡ የከተማይቱም ሰዎች እጅግ ክፉዎች ስለነበሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ ወንጌልን መስበክ አልቻሉም ነበር፡፡ እነርሱም እጅግ ክፉዎች መሆናቸውን ስላወቀ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ዕጣው ሲደርሰው በሀዘን አልቅሶ ነበር፡፡ አሁንም ከተማው በገቡ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ምክንያት በመፍጠር ሮምና ለምትባል ሴት የውሽባ ቤቷ እሳት አንዳጅ ሆኖ አብሮኮሮስም ዕቃ አጣቢ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ የቀጠረቻቸው ሴትም እጅግ ታሠቃያቸው ጀመር፡፡ ባሮቿ እንደሆኑ ተስማምተው ስለጻፉላት ትደበድባቸውም ነበር፡፡
እነርሱም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ እየኖሩ እያለ በአንዲት ዕለት የአገረ ገዥው ልጅ ለመታጠብ ወደ ውሽባው ቤት ገባ፡፡ በውሽባ ቤቱም የሰይጣን ኃይል ስለነበረበት የመኰንኑን ልጅ አንቆ ገደለው፡፡ የአገሪቱም ሰዎች ሁሉ ለሞተው የመኰንን ልጅ ሊያለቅሱ ሲሰበሰቡ ቅዱስ ዮሐንስም አብሮ ቆሞ ሲመለከት ሮምና መጥታ ‹‹በጌታዬ ልጅ ሞት ልትደሰት መጣህን›› እያለች ረገመችው፡፡ እርሱም ‹‹አይዞሽ አትዘኚ›› አላትና ወደ ሞተው ልጅ ቀርቦ በመስቀል ምልክት ካማተበበት በኋላ በፊቱ እፍ አለበት፡፡ የሞተውም ልጅ ድኖ ተነሣ፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች እጅግ ደነገጡ፡፡ ሮምናም ደንግጣ ‹‹እግዚአብሔር የሚሉት አምላክ አንተ ነህን›› ብላ ጠየቀችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹በፍጹም እኔ አምላክ አይደለሁም፣ እኔ የእርሱ አገልጋዩና ሐዋርያው ነኝ እንጂ›› አላት፡፡ ሮምናም ስለበደለቻቸው በደል ሁሉ መሪር ዕንባን እያለቀሰች ይቅር እንዲሏት ለመነቻቸው፡፡ እነርሱም አረጋጉዋት፡፡ ከሕዝቡም ውስጥ ብዙዎቹ በጌታችን አመኑ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ሌሎች ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን እየሰበከ ከጣዖት አገልጋዮች በቀር ሁሉንም አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ አገልጋዮችን ኤጲስቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ከሾመላቸው በኋላ ወደ ሌሎች አቅራቢያ አገሮች ሄደ፡፡
በመጨረሻም በከሃዲውና በጨካኙ በድምጥያኖስ ዘመን በጣዖት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ፡፡ በፈላ ውኃ ካሠቃዩት በኋለ በፍጥሞ ደሴት አጋዙት፡፡ በዚያም ሳለ ራእዩን ተመልክቶ ጻፈው፡፡ ድምጥያኖስም ከተገደለ በኋላ ከግዞቱ ተመልሶ ሦስቱን መልእክታቱንና ቅዱስ ወንጌሉን ጽፏል፡፡ ጌታችንም አስቀድሞ ሞትን እንደማይቀምስ ለዮሐንስ ቃል ገብቶለት ነበርና (ዮሐ 21፡22) ጥር 4 ቀን እንደ ኤልያስና ሄኖክ ሞትን እንዳያይ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወስታል፡፡ ዛሬ ግንቦት 16 ቀንም ዓመታዊ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡ ይኸውም በእስያና በኤፌሶን በዙሪያቸውም ባሉ አገሮች ሁሉ ወንጌልን ስለመስበኩና ስለደረሰበት መከራ ስላደረጋቸውም ብዙ ተአምራት ነው፡፡ ዳግመኛም በእስክንድርያ አገር ቤተ ክርስቲያኑ የከበረችበት ዕለት ነው፡፡
ጌታችን ለዮሐንስ ያልነገረው እርሱም ያላስተማረው ምሥጢር የለም፡፡ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ…›› ብሎ የጌታችን ነገር ተመራምሮ ለመድረስ ሲል በመሀል መልአኩን በዮርዳኖስ ባሕር ላይ ሲሄድ አገኘው፡፡ መልአኩም የዮርዳኖስን ባሕር በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ ውጭ ሲያፈስ ተመለከተው፡፡ ዮሐንስም ተገርሞ ‹‹ምን ማድረግህ ነው›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹የዮርዳኖስን ባሕር ቀድቼ እየደፋሁ ልጨርሰው ነው›› ሲለው ዮሐንስም መልሶ ‹‹ታዲያ በእንቁላል ስባሪ ነውን?›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹አዎን›› አለው፡፡ ዮሐንስም ‹‹በከንቱ ደከምክ›› አለው፡፡ ይህን ጊዜ መልአኩም መልሶ ‹‹አንተስ እንጂ ደግሞ የአምላክን መገኘት፣ አኗኗሩንም ተመራምረህ በጥበብ ለማግኘት ብለህ ‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ..› ብለህ ጀምረህ የለምን? አንተ ጌታን ተመራምረህ ካገኘህና ከደረስክበት እኔም የዮርዳኖስን ወንዝ በዚህ እንቁላል ቅርፊት ቀድቼ እጨርሰዋለሁ›› አለው፡፡ ዮሐንስም ይህን ጊዜ ደንግጦ ዝቅ ብሎ ‹‹ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ…›› ብሎ ሀሳቡን ለወጠና ሌላ ታሪክ ቀጠለ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ወክሎ እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ እርሱም ለመቤታችን በአደራ የተሰጠ ሲሆን እመቤታችንን ከወሰዳት በኋላ ለ16 ዓመት እየተንከባከበ ጠብቋታል፡፡ እናቱም በሕፃንነቱ ስለሞተች እመቤታችን ናት እየተንከባከበች ያሳደገችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልኩም ከጌታችን ጋር ይመሳል ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሥዕል የመሳል ተሰጥኦም ነበረው፡፡ ጌታችን በተሰቀለበት ዘመን የነበረው ጢባርዮስ ቄሳር ልጁ በሽተኛ ነበር፡፡ የጌታችንን የማዳን ሥራ እየሰማ እነ ጲላጦስም ስለጌታችን የሚጽፉለትን ይሰማ ስለነበር ልጁን ከጌታችን መቃብር ላይ እንዲያኖሩለት ላከው፡፡ ልጁም ፈጥኖ ተፈወሰለት፡፡ ጢባርዮስ ቄሳርም በልጁ መዳን ምክንያት የጌታችንን ውለታ ማስቀመጥ ፈልጎ የጌታችንን ሥዕሉን የሚሥልለትን ሲያጠያይቅ ዮሐንስን አገናኙት፡፡ ዮሐንስም ጌታችንን ልክ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ አድርጎ በመሣል ለጢባርዮስ ቄሳር ሰጠው፡፡ ሲሥለውም በመጀመሪያ ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የጌታችን ሥዕልም አፍ አውጥቶ ‹‹በመጀመሪያ አይሁድ
በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?›› ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ ‹‹እንዴት አድርጌ ልሳልህ?›› ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም ‹‹ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ›› አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ከሳለው በኋላ ሥዕሉን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ቢስመው ከንፈሩ አንድ ቀን ተኩል ያህል ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን የጌታችንን ስነ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎች መገኛቸው ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለው ሥዕል ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፡፡ በሕይወቱና በኑሮው ሁሉ ጌታችንን ለመምሰል ይጥር ነበርና ጌታችንም እጅግ ይወደው ስለነበር ‹‹ፍቁረ እግዚእ›› ተባለ፡፡ የታላቁ ያዕቆብ ታናሽ ወንድም ስለሆነና አባቱም ዘብድዮስ ስለሚባል ‹‹ዮሐንስ ወልደ ዘብድዮስ›› ተባለ፡፡ ለጌታችን ባለው ቅናትና ከወንድሙ ጋር ሆነው ባሳዩት የኃይል ሥራ እንዲሁም የጌታችንን አምላክነት በመግለጡ ‹‹ወልደ ነጎድጓድ›› ተብሏል፡፡ ነገረ መለኮትን ከሌሎቹ በበለጠ ሁኔታ አስፍቶና አምልቶ በማስተማሩ ‹‹ነባቤ መነኮት ወይም ታኦሎጎስ›› ተብሏል፡፡ ኃላፊውንና መጻዒውን ጊዜ በራእዩ ስለገለጠ ‹‹አቡቀለምሲስ›› ተባለ፣ ይህም በግሪክኛ ባለራእይ ማለት ነው፡፡ የጌታችንን መከራ መስቀሉን እያስታወሰ 70 ዘመን ሙሉ እያለቀሰ ስለኖረና ፊቱም በሀዘን ስለተቋጠረ ‹‹ቁዱረ ገጽ›› ተብሏል፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡ (ምንጭ፡- ስንክሳር ዘወርሃ ጥር፣ ቤተ ክርስቲያንህን ዕወቅ፣ የቅዱሳን ታሪክ-30)
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን ዕውቀትን ከልቡ ያፈለቀ የኢየሩሳሌሙ ሰው የአልዓዛር ልጅ ኢያሱ ሢራክ አረፈ። እርሱም በጥንተ ትንቢቱ የባሕር አሸዋን የዝናም ጠብታን የዘመንን ቁጥር ማን ቈጠረ አለ።
ከአብ ጋራ ስለ አለው አንድነት የጥበብ አኗኗር ከዓለም መፈጠር በፊት ነው ለጥበብ መገኛዋ ለማን ተገለጠ የጥበብ ምክሯንስ ማን አወቀ በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ የምትቀመጥ እጅግ የምታስፈራ ናት አለ።
ሁለተኛም እኔ ከልዑል አፍ ወጥቼ ምድርን አንደ ጉም ሸፍንኋት በሰማያትም እኖራለሁ ዙፋኔንም በደመና ምሰሶ ላይ ዘረጋሁ ብቻዬን በሰማይ ዳርቻ ዞርኩ በውቅያኖስም ጥልቅ ውስጥ ማረፊያ እየፈለግሁ በባሕሩ ውኃ ላይ ሁሉ ተመላለስኩ አለች አለ።
ስለ ወልደ እግዚአብሔርም ሰው መሆን እንዲህ አለ እግዚአብሔር በያዕቆብ ዘንድ እደሪ በእስራኤልም ዘንድ ተዋረሺ አለኝ አለች። ደግሞ ስለ መድኃኒታችን ሞትና ስለ አይሁድ መጥፋት በወጥመዱ ይጠመዳሉ የመሞቻቸው ጊዜም ሳይደርስ ይሠጥማሉ አለ። ስለ ንስሓና ከንስሓ በኋላ ወደ ኃጢአት ስለ መመለስ እንዲህ አለ ከታጠቡ በኋላ ቆሻሻን መዳሰስ ምን ይጠቅማል።
ደግሞ ስለ ቤተክርስቲያን መታነፅና ስለ ሕዝብ እንዲህ አለ። አቤቱ በስምህ የተጠሩና በበረከት ያባዛኃቸውን ወገኖችህን ይቅር በል መመስገኛህና ማደሪያህ የሆነች ሀገርህ ኢየሩሳሌምንም ይቅር በል። የቃልህንም በረከት በጽዮንና በልጆቿ ላይ ምላ።
ስለሹማምንትና ስለ ሰባቱ መዐርጋት ሲናገር እንዲህ አለ ሰባቱን ኃይሎች የተቀበለች የሰው ሰውነቱ ጉበኛ ናት። ከዚህም ሁሉ ጋር መንገድህን ያቀናልህ ዘንድ ወደ ልዑል እግዚአብሔር ጸልይ። ስለ ጻድቃንም እንዲህ አለ የጻድቃን ልጆች በዱር ጠል የዱር አበባ እንዲ አብብ እንዲሁ ብቀሉ አብቡም እንደ ሊባኖስም መዓዛ መዓዛችሁ እንዲሁ የጣፈጠ ይሁን።
ዳግመኛም የእግዚአብሔርን ሥራ ሲያስብ እንዲህ አለ የሰማይን ንጽሕናውንና ጽናቱን ብርሃኑንም ያሳይ ዘንድ በሰማይ ገጽ ላይ ፀሐይን ማውጣቱን በቀትርም ጊዜ አገሩን ማቃጠሉን አስቦ። እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ላቦቱን ማን ይቃወመዋል የፀሐይ ዋዕይ ሦስተኛውም ተራሮችን ያቃጥላቸዋል ከእርሱም የእሳት ወላፈን ይወጣል አለ።
ጨረቃም ለዓለም ምልክቱ ነው በእርሱም የዘመናት የበዓላት ምልክት ይታወቃል። ስለ ከዋክብትም የሰማይ ጌጦቿ የከዋክብት ብርሃናቸው ነው በእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ እንዲሁ ያበራሉና በሥርዓታቸውም ጸንተው ከልካቸውም ሳይፋለሱ ሳይሳሳቱ ጸንተው ይኖራሉና አለ።
ስለ ቀስተ ደመናም ተናገረ ቀስቱን አየሁ ፈጣሪውንም አከበረ ብርሃኑ መልካም ነውና የልዑል ሥልጣንም ያዘጋጀዋል። ስለ በረድና መብረቅም ተናገረ ስለ እርሱ ትእዛዝም በረድ ይዘንማል በቃሉም መብረቅ ይፈጥናል ደመናትም እንደ አዕዋፍ ይበራሉ ነፋስም በእርሱ ፈቃድ ይነፍሳል የነጐድጓድ ድምፅና ብልጭልጭታው ምድርን ያስፈራታል ዐውሎውና ውርጩ ነፍስን ያስጨንቃታል።
ሰማይን እንደ ብረት ልብስ የሚሸፍነው እንደ ስለታም የብርጭቆ ስባሪ ይብለጨለጫል አለ። ስለ ዝናምም ተናገረ ዝናም የወረደ እንደሆነ ምድርን ድስ ያሰኛታል በትእዛዙም ባሕር ይደርቃል አለ። አባቶችንም በተሰጣቸው ሀብት ሲያመሰግናቸው ኄኖክ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘው። ኖኅም ጻድቅ ሁኖ እንደተገኘ።
አብርሃም ታማኝ እንደሆነ ይስሐቅም ለሰው ሁሉ የሚጠቅም በረከት እንደተሰጠው ለያዕቆብም በቸርነቱ እንደ ተገለጠለት ዐሥራ ሁለቱንም ነገድ እንደወለዳቸው በሰውና በእግዚአብሔርም ዘንድ እንደ ተወደዱ። ሙሴንም ስም አጠራሩ የከበረ የምላእክትም ብርሃን መልኩና ስም አጠራሩ የሆነ አለ። ወንድሙ አሮንንም የዘላለም ሕግን እንደ ሠራለት በልብሰ ተክህኖና በወርቅ አክሊል እንዳስደነቀው አለ። ሹመቱ ሦስተኛ የሚሆን የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስንም ወደሰ።
የነዌ ልጅ ኢያሱን ለእስራኤል ልጆች የርስታቸውን ምድር እንዳወረሳቸው እጁንም በአነሣ ጊዜ እንደተመሰገነ። ሳሙኤልንም በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ እንደሆነ ናታንንም በዳዊት ዘመን ትንቢት እንደተናገረ። ዳዊትንም ታናሽ ሁኖ ሳለ አርበኛውን ጎልያድን እንደገደለው አምስግኖታል ሰሎሞንንም በሰላም ወራት እንደነገሠ።
ኤልያስንም ሙት እንዳስነሣ እሳትንም ከሰማይ እንዳወረደ ራሱም በእሳት ሠረገላና በእሳት ፈረሶች እንደዐረገ። ኤልሳዕንም በዘመኑ ጠላቶች እንዳስደነገጡት ሁለት ሙታኖችንም እንዳስነሣ አንዱን በሕይወት ሳለ አንዱን ከሞተ በኋላ።
ሕዝቅያስንም አገሩን አጽንቶ እንደ ጠበቀ የፋርስንም ሠራዊት በጸሎቱ አጥፍቶ ስለ ሀገራቸው ጽዮን የሚያለቅሱትን ደስ እንዳሰኛቸው ርኵሰትንና ኃጢአትንም እንደ አስወገደ ኢዮስያስንም የኢዮስያስ ስም አጠራሩ መልካም ነው እንዳለው።
ኤርምያስንም ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ እንዳከበረው። ሕዝቅኤልም የእግዚአብሔርን ጌትነቱን እንዳየ። ዘሩባቤልንም በቀኝ እጅ እንዳለ ኀቲም ቀለበት ነው እንዳለው።
ዐሥራ ሁለቱ ነቢያትንም በየቦታቸው ዐፅማቸው እንደሚለመልም። ሆሴዕና ነህምያንም የወደቀች ቅጽርን አንሥተው ጠቃሚ ሥራ እንደሠሩ። ዮሴፍንም እርሱን የመሰለ ደግ ሰው እንዳልተወለደ። ኖኅና ሴምንም ክብራቸው ከሰው ሁሉ እንደሚበልጥ። አዳምንም በፍጥረት ሁሉ ላይ ንጉሥ እንደ ሆነ።
ስምዖንን በዘመኑ ቤተ መቅደስ እንደታነፀ በሕዝቡ ከምርኮ መመለስም እንደ ተመሰገነ በመጽሐፉ መጨረሻም። በሁሉ ቦታ ታላላቅ ሥራ የሚሠራና ዕድሜያችንን የሚያስረዝም እግዚአብሔር አምላክን አመስግኑት አለ። ይህንንም ተናግሮ በፍቅር አንድነት አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ለአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም ከሞት ተሰወሩ፡፡ አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ የትውልድ ሀገራቸው ሸዋ መርሐ ቤቴ ነው፡፡ እንደ እነ ኤልያስና ሄኖክ ተሰውረዋል እንጂ በምድር ላይ ሞትን አልቀመሱም፣ ገና ወደፊት መጥተው በሰማዕትነት ይሞታሉ፡፡ ልደታቸው ሐምሌ 16 ቀን ነው፡፡ የነበሩበት ዘመንም በጻድቁ ንጉሥ በዐፄ ገብረ ማርያም ሐርበይ ዘመን ነው፡፡ ጻድቁን መልአኩ ከሚያገለግሉበት ከወሎ የህላ ሚካኤል ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ወስዷቸው እንዲመነኩሱ አድርጓቸዋል፡፡ የቆረቆሩት ‹‹አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ ገዳም›› ወሎ መሐል ተከዜ ውስጥ ይገኛል፡፡ የበዛው ገድላቸው በዝርዝር ተጽፎ አይገኝም፡፡ ተከዜ በረሃ ላይ እጅግ አስደናቂ ትልቅ የአንድነት ገዳም አላቸው፡፡ 12 ክንፍ የተሰጣቸው ታላቁ ጻድቅ አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ በዛሬዋ ዕለት ነው የተሠወሩት፡፡
🗓 ግንቦት 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ (ስብከቱና ቅዳሴ ቤቱ)
2.ቅዱስ ኢያሱ ሲራክ ነቢይና ጠቢብ (መጽሐፈ ሲራክን የጻፈ)
3.ቅድስት እናታችን ዐስበ ሚካኤል (ኢትዮዽያዊት)
🗓 ወርኀዊ በዓላት
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ
(የቅዱስ ላሊበላ ወንድም)
4.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
7.አባ ዳንኤል ጻድቅ
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
( እና )