Think Ethiopia

Think Ethiopia

Share

የሀገርኛ መፅሐፍት አጭር ዳሰሳ እና ደረጃ ያገኛሉ።

20/06/2026

የአቶ ሰይፉ መታፈሪያ የሥነግጥም መድብሎች፣ የጥናት እና የምርምር ሥራዎች እና ለኢትዮጵያ የፎክሎር ጥናት እና ለአማርኛ ቋንቋ ዳብሮት ያበረከቱት አስተዋጽኦ

አቶ ሰይፉ መታፈሪያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው 17ኛው ዓለማቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባኤ፣ አቃቂ ግቢ (Nov. 2-5, 2009)

የዕውቁ ገጣሚ፣ መምህር እና የፎክሎር ባለሙያ የሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው መታሰቢያ ልዩ ዝግጅት ላይ በቪዲዮ ተቀርፆ የቀረበ።የካቲት 19 ቀን፣ 2014 ዓ.ም. [February 26 2022]



የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም፣ ራስ መኰንን አዳራሽ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ኢትዮጵያ።



ሰላም፣ ጤና ይስጥኝ! የተከበራችሁ የአቶ ሰይፉ ቤተሰቦች፣ ክብርት እናታችን ወ/ሮ አማረች መንግሥቱ፣ እኅታችን ወ/ሮ ሠምራ ሰይፉ መታፈሪያ፣ የተከበራችሁ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፣ የአቶ ሰይፉ መታፈሪያ የሥራ ባልደረቦች፣ የቀድሞ ተማሪዎች እና የሥነግጥም አፍቃሪዎች፣ ክቡር ዶ/ር ታከለ መርእድ፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ ዳይሬክተር፣ ክቡራን እና ክቡራት፤

በቅድሚያ በዛሬው ዕለት ለታላቁ ገጣሚ፣ መምህር እና የፎክሎር ተመራማሪ ለአቶ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ልዩ የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ በአካል መገኘት ባልችልም፣ ከቤተሰባቸው ጋር በመመካከር አጭር የቪዲዮ መልእክት እንዳስተላልፍ ስለተፈቀደልኝ ከልቤ አመሰግናለሁ።

ከቤተሰቦቻቸው እንደሰማችሁት፣ ዛሬ የአቶ ሰይፉ መታፈሪያን ሕይወት፣ የሥነ ግጥም መድብሎቻቸውን እና የጥናት እና የምርምር ሥራዎቻቸውን የምንዘክርበት ልዩ የመታሰቢያ ዝግጅት ነው።

አቶ ሰይፉ እጅግ የማደንቃቸው የቀለም አባቴ፣ መምህሬ፣ አማካሪዬ፣ እና ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሥራ ባልደረባዬ፣ እንዲሁም ለበርካታ ዓመታት እጅግ የማከብራቸው ወዳጄ ናቸው።

እንደ ቤቴ ብለው በሚያዩት እና ከ50 ዓመታት በላይ ባስተማሩበት እና በተመራመሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት የመታሰቢያ መርሐ ግብር ስለተዘጋጀላቸው እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል።

ንግግሬን በአራት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

1. ዕውቁ ገጣሚ ሰይፉ መታፈሪያ እና የግጥም መድብሎቻቸው

2. መምህሩ እና የፎክሎር ተመራማሪው ሰይፉ መታፈሪያ

3. ሰይፉ መታፈሪያ ለአማርኛ ቋንቋ ዳብሮት ያበረከቱት አስተዋጽኦ

4. ሰይፉ መታፈሪያን እና ሥራዎቻቸውን ወደፊት እንዴት እናስታውሳቸው?

1. ዕውቁ ገጣሚ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው እና የግጥም መድብሎቻቸው

ገጣሚ፣ መምህር እና የፎክሎር ተመራማሪ የሆኑት ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው በኢትዮጵያ ውስጥ አንቱ ከሚባሉ አንጋፋ ምሁራን እና ስመጥር ገጣሚያን መካከል አንዱ ናቸው። ሰይፉ መታፈሪያ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በሀገራችን ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የፎክሎር እና የሥነ ጽሑፍ ተማሪዎችን እና ምሁራንን አፍርተዋል። የሥነ ግጥም የፈጠራ ጥበባቸውን እና አሻራቸውን በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በወጣት ገጣሚያን ላይ እንዳሳረፉ ከልዩ ልዩ የግጥም እና የጃዝ ምሽት ዝግጅቶች፣ የግጥም ንባብ እና የውይይት መድረኮች መረዳት እንችላለን። በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ ሀገር ወደዚች ዓለም የመጡት ሰይፉ መታፈሪያ በግጥም ሥራዎቻቸው፣ እጅግ በርካታ እና ረቂቅ ሐሳቦችን አንሥተው የጻፉ፣ እሳቸው እንደሚሉት “ዘራእንስሳን እና ዘራተፈጥሮን” የሕይወትን ምስቅልቅል በግጥሞቻቸው ውብ አድርገው በተመረጡ ቃላት እና ስሜትን ሰቅዘው በሚይዙ ስንኞች ያቀረቡልን ገጣሚ ናቸው። አቶ ሰይፉ እንደሚነግሩን

በረጅሙ የመምህርነት ዘመናቸው በሐረር እና በአዲስ አበባ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በካርቱም ዩኒቨርሲቲ አማርኛ፣ ሥነግጥም፣ ፎክሎር፣ ሥነቃል፣ በሳል ድርሰት፣ የጥናት የምርምር ርእስ መረጣ ሴሚናር፣ ወዘተ. የተባሉ ኮርሶችን አስተምረዋል።

የአቶ ሰይፉ ሥነጥበባዊ ሕይወት እሳቸው እንደሚሉት “ጠቅላላውን ከድርሰት በተለይም ከሥነግጥም አባዜ፣ ልክፍት-በሽታ ጋራ የተሳሰረ ነው። የሕይወትን (የዘራሰብን እና የዘራንስሳን) የትመጣ ለማወቅ ወይም ለመረዳት መነሻውን፣ እኔነቱን፣ አኪያኼዱንና መድረሻውን፣ ከራሳቸው ውስጣዊ ሰብእና፣ ዓይነልቦና እና ጥልቅ ተመስጦ ጋር እጅጉን ያጣምሩታል። ሰይፉ መታፈሪያ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በኢትዮጵያ እጅግ የተለየ የግጥም አጻጻፍ ስልትን ያስተዋወቁና ያስፋፉ ዕውቅ ገጣሚ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት የግጥማቸው የአጻጻፍ (ዓይነት) „በብዙ ረገድ ባህል-ከተል አይደለም። በዚህ

ያጻጻፍ አዲስነት አስገዳጅነትም ስም ስላስፈለገው „ስንኝ አጠፍ ግጥም“ የሚል ስያሜ ሰጥተውታል።(1995)
የሰይፉ መታፈሪያ የሥነግጥም መድብሎች በርካታ የሥነጽሑፍ ምሁራንን አስተውሎት የሳቡ ሲሆን ለብዙ የጥናት እና የምርምር ጽሑፎች ዋና መሠረት በመሆን ለምሁራዊ ውይይት እና ክርክር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ወደፊትም ያደርጋሉ። ሰይፉ መታፈሪያ ከ1964 እስከ 2001 ባሉት ጊዜያት ስድስት የሥነግጥም መድብሎችን አሳትመዋል። በታተሙት መድበሎቻቸው ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ልዩና ውብ ግጥሞችን ደርሰዋል። በግጥሞቻቸው ውስጥ ትኩረታቸውን እና ዓይነ ልቦናቸውን ከሳቧቸው ዋና ዋና ርእስቶች መካከል፣ ሕይወት፣ ተፈጥሮ፣ ዘራስሳት እና ዘራፅዋት፣ እኔነትና ሰዋዊ መስተጋብር፣ የገጣሚ ጭንቀት፣ የዕለት ተለት ረቂቅ ቅጽበቶች፣ ወዘተ. ይገኙበታል። እነዚህን ውብ እና አመራማሪ ግጥሞች ማንኛውም ሰው እንዲረዳቸው ካስፈለገ፣ የአቶ ሰይፉን ሰብእና፣ በተለይም ለሰው ልጅ እና ለሕይወት ያላቸውን እጅግ ደግነት፣ ሩሕሩሕነት እና ቅን አሳቢነት ማወቁ አስፈላጊ ይመስለኛል። ይኸ ደግሞ ቀላል አይደለም። ምክያንያቱም የሕይወት ታሪካቸው፣ ልዩ የቋንቋ ፈጠራ ጥበባቸው እና ችሎታቸው በዝርዝር አልተጻፈምና። ይኸ ወደፊት ከቤተሰባቸው፣ ከቅርብ ጓደኞቻቸው እና ወዳጆቻቸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው እና ከተማሪዎቻቸው ጋር በቅርበት በመመካከር የሚጠናቀር ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡

ከቅርፅ አንጻር፣ የአቶ ሰይፉ ልዩ የግጥም ሐሳብ ወይም ጭብጥ ከሁለት መሥመር ስንኝ ማለትም፣ “ገጣሚ ሲቆጣ” (ዐባይ ፈንጆ የቀበረ ውኀ፣ 2001 ዓ.ም. ገጽ፣ 116) ከሚለው ግጥም አንሥቶ “የመተሐራው ባላባት” እስከሚለው ረጅም እና ባለ 15 ገጽ ግጥማቸው (ዐፈር ያነሣ ሥጋ፣ 1964 ዓ.ም፣ ገጽ፣ 41-55 ድረስ ይዘልቃል።

ገጣሚ ሲቆጣ፣

መጻፍ፣ መጻፍ አለኝ ማቅለም ወረቀት፣
ብእሬን ማስቆጣት ቀይ ደም ማስተፋት።

አቶ ሰይፉ እንደሚሉት “የግጥም ጭብጥ የተዳፈነ እሳት ነው። ከልብ አይጠፋም። ቆይቶ፣ ቆይቶ አንድ ቀን ቦግ ይላል። “የተፈጥሮ እርስበርስዋ” ግጥም ጉዳይም እንዲያ ያለ ነበር። የ1990 ፈረንጅ ዓመት (ፈ.ዓ.) የመጀመሪያው ንድፍ አልጥም ብሎኝ ከተውኩት በኋላ፣ ቆይቶ ቆይቶ፣ ባንድ ባላሰብኩት – ምክንያት አግኝቶ – ቀጨም! አረገኝ። ገጣሚ የመጣልኝ (inspiration) ባሪያ ነው፣ ስለዚህም ግጥም የሚያስጽፍ ገጠመኝ ሲመጣበት ወይም ሲመጣለት፣ ያለው ምርጫ “እሺ!” ብሎ መጻፍ ብቻ ነው። እና መጻፍ ጀመርኩ – ከ1990 እስከ 2000 ፈ.ዓ. በያዝ ለቀቅ ዓይነት አንቀራበጥሁት” ይሉናል። (ከራስ ድንበር ባሻገር፣ 2003 ፈ.ዓ.፣ ገጽ፣ VI)

ሰይፉ መታፈሪያ የገጣሚን ወይም የባለቅኔን ጭብጥና ጭንቀት በሚመለከት በተለይ ዐባይ ፈንጂ የቀበረ ውኀ (2001 ዓ.ም.) በተሰኘው መድብላቸው ብቻ፣ የሚከተሉትን ርእሶች መርጠው አእምሮን አመራማሪ፣ ስሜትን ኮርኳሪና መሳጭ ግጥሞችን ጽፈዋል።

1. እይታ ያባነነው ገጣሚ (ገጽ፣ 61)

2. ገጣሚ አለፈ (ገጽ፣ 224)

3. ገጣሚ (ገጽ፣ 237)

4. ነፍሰ ገዳዩ ገጣሚ (ገጽ፣ 243)

5. ገጣሚ ሲለከፍ (ገጽ፣ 289)

6. ገጣሚነት ጭንቁ (ገጽ፣ 505)

7. የግጥም ቃልኪዳን (ገጽ፣ 556)

በአቶ ሰይፉ መድብሎች ውስጥ በልዩ አሰነኛኘት ስልት የተደረደሩት ግጥሞችና የገጽ ብዛት ማሳተም ከጀመሩበት ዘመን ከ1964 ዓ.ም. አንሥቶ እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ እያደገ ይመጣል፣- ማለትም፣ ከ84 (ውስጠት) ወደ 608 (ዐባይ ፈንጅ የቀበረ ውኀ)።

2. መምህሩ እና የፎክሎር ተመራማሪው ሰይፉ መታፈሪያ

ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው በፎክሎር /ሥነቃል የጥናት መስክ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የድኅረ ምረቃ ተመራቂ እና ምሁር እንደሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለዚሁም እ.ኤ.አ. በ1978/79 በካርቱም ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍሪቃ እና የእስያ ጥናት ተቋም፣ ለፎክሎር የትምህርት ክፍል ለማስትሬትያቀረቡት እጅግ ጥልቅ የሆነው የጥናትና የምርምር ሥራቸው ነው። ይህንን የጥናት እና የምርምር ሥራ በቀድሞው የምሥራቅ ሐረርጌ ክፍለ ሀገር፣ በተለያዩ የገጠር አካባቢዎች ተዘዋውረው የመስክ ጥናት በማከናወን የገበሬዎችን ልዩ ልዩ የሥራ ዘፈኖች፣ ግጥሞችና ዜማዎች ከኦሮምኛ ወደ እንግሊዝኛ በመተርጐምና ሰፊ ሐተታ በማካተት ያዘጋጁት ጥልቅ የጥናት እና የምርምር ሥራ ነው። ይህ ጥናት በቅርቡ ለሕትመት እንደሚበቃ ተስፋ አለኝ። ጋሽ ሰይፉ የፎክሎርን የዕውቀትና የጥናት መስክ በጥልቀት በማጥናት፣ በመመርመር እና በማስተማር፣ እንዲሁም ወጥነት ያለው የምርምር ጥናት በማካኼድ “የፎክሎር መዝገበ -ቃላት ጥንቀራ ቅድመ ዝግጅት” በሚል ርእስ በኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት Journal of Ethiopian Studies (1993) ላይ ያሳተሙት ረዥም የምርምር ጽሑፍ በዋናነት

ተጠቃሽ ነው። ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ ልዩ ልዩ የፎክሎር ሙያ-ነክ ቃላትን በመሰብሰብ፣ በመፍጠር፣ ክያኔያዊ እና ዐውዳዊ ብያኔ በመስጠት የጥናት መስኩ ወጥነት እንዲኖረው ያቀረቡት እጅግ የሚደነቅ የምርምር ውጤት ነው። በመጽሐፍ መልክ የማሳተም ዕቅድ

እንደነበራቸው ነግረውኛል። ለምሳሌ፣ ተረትን በሚመለክት የፈጠሯቸውን ሙያ-ነክ ቃላት እንደሚከተለው ያቀርቡልናል፣ ተረታተረት (tales)፣ አድባሬ ተረት (fairy tale)፣ ሞኜ ተረት (noodle story)፣ እንስሴ ተረት (animal tale) ወዘተ.።
አቶ ሰይፉ በተለያዩ የሥነቃል ዘርፎች (ቃል ግጥም፣ ምሳሌያዊ አነጋገር፣ ተረቶች፣ ወዘተ.) ላይ በርካታ የጥናት እና የምርምር ሥራዎችን በማዘጋጀት በተለያዩ ዓለማቀፍ የጥናት እና የምርምር መጽሔቶች ላይ ያሳተሙ ታላቅ ምሁር ናቸው።

3. ሰይፉ መታፈሪያ ለአማርኛ ቋንቋ ዳብሮት ያበረከቱት አስተዋጽኦ

አቶ ሰይፉ በርካታ ያገራችንን እና የአውሮጳን ቋንቋዎች አጥርተው የሚናገሩ እና ጠንቅቀው የሚያውቁ ልሳነ ብዙ ምሁርና ተመራማሪ ናቸው። አማርኛ፣ ግዕዝ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማልኛ፣ ዐረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ግሪክኛ፣ ላቲን፣ እና ጣሊያንኛ ቋንቋዎችን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ጀርመንኛንም በመጠኑ ያውቁ ነበር። ይኸው ልዩ የቋንቋ ተሰጥዖአቸውም አዳዲስ ሙያ-ነክ ቃላትን በመፍጠር ያማርኛን ቋንቋ በማሳደግ እና ለማኅበረሰባችን በማስተዋወቅ ረገድ እጅግ የላቀ ሚና የተጫወቱ ምሁር ናቸው። ለዚህም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ „ብእሮጋዊ መግቢያ“ (introductory essay) በሚል ርእስ ለሥነግጥም መድብሎቻቸው የጻፏቸውን ረዣዥም ጽሑፎች እና ያሳተሟቸውን ምርምራዊ መጣጥፎች (1993) ማመሳከር ይቻላል።

የአቶ ሰይፉ እጅግ የተለየ የቋንቋ ተሰጥኦ አዳዲስ ቃላትን የመፍጠር ልዩ ችሎታቸው ነው። ይኸንን አስመልክተው ገጣሚው እንዲህ ይሉናል። „በብዙዎቹ ግጥሞቼ ውስጥ ተውሼ፣ ፈጥሬ፣ ወይም ጨፍልቄ እምጠቀምባቸው አማርኛ ቃላት፣ አንባቢን እንደሚያነጫንጭ ዐውቃለሁ፤ የግጥም አጻጻፍ ስልቴ አስገድዶኝ ነው፤ ይህን ማድረጉ ደግሞ ላማርኛ ዳብሮት ያለኝን ጉጉት ያረካልኛል። … ፍጥርና ጭፍልቅ ቃሎቼ ካማርኛ ሕግ እስከዚህም የራቁ አለመሆናቸው ይታያል።“ (1995)

አቶ ሰይፉ ለፈጠሯቸው አዳዲስ ቃላት ሰፊ ማብራሪያ እና አንዳንድ ጊዜም ከእንግሊዝኛ አቻቸው ጋር የሚጽፉት “ሙዳዬ ቃላት” ወይም (Glossary) ብለው በመጽሐፎቻቸው መጨረሻ ላይ በሚያቀርቡት ርእስ ሥር ነው።

በሥነ ጽሑፍ ተማሪዎቻቸው እና በተመራማሪዎች ዘንድ በስፋት የሚደነቁላቸው እርሳቸው የፈጠሯቸው ሙያነክ ቃላት፣ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት በሥነግጥም መድብሎቻቸው ውስጥ ካስተዋወቋቸው አዳዲስ ቃላት መካከል አንዳንዶቹን ለአብነት ያህል እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

መጣጥፍ፣ በሳል ድርሰት፣ ትየባ፣ ተዝናኖት፣ ትጥበት፣ ኑረት፣ ሩጠት፣ ጡፈት፣ ውስጠት፣ ዝልቀት፣ ቃላውድ (context) ፣ ማወነት (እውነት ማድረግ)፣ ሰባትካት (የጥንት ዘመን ሰዎች)፣ አብሮነት፣ አብሮኛ ብ.ቍ. አብሮኞች (የሕይወት ተጋሪ፣ አብሮ ሆኖ የተገኘ)፣

እንጃኝልሽ (“እንጃኝልሽ ንቢት” ግጥም ውስጥ)፣ አንተየሻ (አንተ ሆዬ)፣ ተመስጦ፣ አበርክቶ፣ ተስተላልፎ፣ ተዋስጦ፣ አስተናግዶ፣ ሥንከን (art)፣ ሠንካኝ፣ ምጥቃለም (space)፣ ኅብራድምፅ (sound harmony) ሠረወ፣ ሥርወት (etymology) ምታመት፣ ዐይነልቦና (imagination) መልሰኛ፣ መርካቶኛ፣ እንጃማሞች (እንጃ ባዮች)፣ ጆሌ ቢያ (ያገር ልጅ፣ ከእንግሊዝኛ)፣ ስጆግ (መጆግ) በእግሬ ስኼድ፣ ባቦት (nostalgia)፣ መጣልኝ (inspiration)፣ ቆምታ (pause) ወዘተ. ይገኙበታል። አቶ ሰይፉ የፈጠሯቸውን አዳዲስ ቃላት በጥንቃቄ ሰብስቦ በሚገባ ማጥናት እና ፈለጋቸውን መከተል ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ።

በተጨማሪም በ1980ዎቹ ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የባሕል እና የትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት በዚያን ጊዜው የባህል ሚኒስቴር ሥር በነበረው የ“ኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ” በተካኼደው “የሳይንስና ቴክኖሎጂ የቃላት ሥያሜ እና ትርጉም ፕሮጀክት” ውስጥ በአማካሪነት እና በዋና አዘጋጅነት ተሳትፈዋል። ሰይፉ መታፈሪያ በዚህ ሙያዊ የቃላት ፈጠራ እና የትርጕም ፕሮጀክት ውስጥ ሰፊ የቋንቋ ክሂሎታቸውንም ለሌሎች ምሁራን በማካፈል፣ ለአማርኛ ቋንቋ ዳብሮት እና ዘመናዊነት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ የሥያሜ ቃላት ሥራዎችን ሠርተዋል፣ የአተረጓጐም ስልቶችን እና ዘዴዎችን አስተዋውቀዋል።

ሰይፉ መታፈሪያ አብዛኛውን ሕይወታቸውን በመምህርትነት ሙያ ላይ ቢያሳልፉም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ በዋና ጸሐፊነት አገልግለዋል። በተለይም በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ በአዲስ አበባ የተደረገውን የምሥራቃዊ ወይም የ“ኦሬንታል” አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ጉባዔ በማስተባበር እና በማዘጋጀት የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

4. ሰይፉ መታፈሪያን እና ሥራዎቻቸውን ወደፊት እንዴት እናስታውሳቸው?

ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው በአሁኑ እና በወደፊቱ ትውልድ እንዴት ይታሰባሉ? ለአቶ ሰይፉ የሥነግጥም አሻራ ሕያውነት፣ ለቋንቋ እና ባህል ጥናት ልፋታቸው መታሰቢያነት አስፈላጊ ናቸው ብዬ ያዘጋጀኋቸውን ሐሳቦች እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

1. እስካሁን ድረስ ያልታተሙ ሦስት የሥነግጥም መድብሎቻቸውን ማሳተም፣ እነዚህም

1.1. የወዲያው በኩል፣
1.2. ዋዜማ፣
1.3. ???

2. ያልታተሙ የትርጕም እና የምርምር ሥራዎቻቸውን ማሳተም፤

2.1. እላይ የጠቀስሁት ከምሥራቅ ሐረርጌ ማኅበረሰቦች ሰብስበው ያጠኗቸውን በርካታ የሥራ ግጥሞች፣ ዘፈኖች፣ ዜማዎች፣ ምርቃቶች፣ ወዘተ. እና ለካርቱም ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ እና እስያ ጥናት ተቋም፣ የፎክሎር የትምህርት ክፍል ያቀረቡትን ጥልቅ የምርምር ጥናት ማሳተም፣

2.2. ከእንግሊዝኛና /ከግሪክኛ ወደ አማርኛ የተረጐሙትን የሐተታማልክት መጽሐፍ ማሳተም፣

2.3. የዕለትውሎ ማስታዎሻዎቻቸው እና ከተለያዩ ወዳጆቻቸው ጋር የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎች ከሕይወት ታሪካቸው ጋር ባንድ ቅጽ ማሳተም፣

3. አቶ ሰይፉ ለአማርኛ ቋንቋ ዳብሮት ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ዕውቅና እና አክብሮት በመስጠት፣ ከተቻለ እና ጥሩ የሥነ ጽሑፍ ተሰጥኦ ያለው ተርጓሚ ከተገኘ ከስድስቱ መድብሎቻቸው ውስጥ የተወሰኑ ግጥሞችን መርጦ ወደ እንግሊዝኛ በመተርጐም አንድ የሥነ ግጥም መድብል አሳትሞ ለዓለማቀፍ አንባቢያን ማቅረብ፣

4. ለአቶ ሰይፉ መታፈሪያ መታሰቢያ፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመመካከር የታላቁን የጥበብ ሰው፣ የዕውቁን ገጣሚ እና መምህር ዝክረ ሕይወት በማስታወስ ጥቅምት 24 ከተቻለ እና ዐቅም በፈቀደ መጠን በያመቱ የሥነግጥም እና የውይይት ሲምፖዚዬም ማዘጋጀት የሚሉ ናቸው።

ክቡራን እና ክቡራት፣ በመጨረሻም፣ ስለ ታላቁ የቀለም አባቴ፣ ስለ አቶ ሰይፉ አንዳንድ የግል ገጠመኞችን ባጭሩ እንደሚከተለው በማቅረብ ንግግሬን አጠናቅቃለሁ።

አቶ ሰይፉን እኔ እንደማውቃቸው፤

1. ለሰው ልጅ እጅግ አዛኝ፣ አሳቢ፣ ሩኅሩኅ እና ሰው አክባሪ ናቸው።
2. ፊታቸው ሁልጊዜ በፈገግታ እና በሣቅ የተሞላ ነው። ንግግራቸው እጅግ መሳጭ በሆኑ ምሳሌያዊ አነጋገሮች እና ውብ ቃላት የተሞላ ነው።
3. አቶ ሰይፉ “ፎክሎር በውስጤ አለ” ብለው የሚያምኑ፣ ይኸንንም በተግባር ያሳዩ መምህር፣ ተመራማሪ እና ምሁር ናቸው። ለመምህርነት ሙያቸው እና ለተማሪዎቻቸው እጅግ ከፍተኛ አክብሮት፣ ጭንቀት እና ፍቅር ያላቸው ናቸው።
4. በደስታ፣ በአክብሮት እና በፍቅር የተሞላው “የትዳር ሕይወታቸው አርአያነት ያለው ነው። ከባለቤታቸው ከወ/ሮ አማረች፣ እሳቸው “አሚ” በሚል የቁልምጫ ስም ከሚጠሯቸው እጅግ ደግ የትዳር አጋራቸው ጋር እንደ “እኅትና ወንድም”፣ እንደ “እናትና አባት”፣ እንደ “ጓደኛ” ሆነው በፍቅር እና በስስት የሚተያዩ አርአያ ወላጆች እና ቤተሰቦች ሆነው በማየቴ እጅግ ዕድለኛ እና ደስተኛ ነኝ። ይኸንንም ልዩ የትዳር እና የፍቅር ሕይወት በግጥሞቻቸው ከማሳየታቸውም በተጨማሪ አሜሪካ አገር በኖሩባቸው ዓመታት፣ በአትላንታ ጆርጂያ ለኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አባላት፣ ለወጣቶች እና ለታዳጊዎች እንዲሁም ለቤተሰቦች በመምክር እና በማስተማር ሰፊ የሕይወት ተሞክሯቸውን ሳይሰስቱ አካፍለዋል። ከፍተኛ አክብሮት እና አድናቆትም ተችሯቸዋል ።
5. አቶ ሰይፉ ጸሎተኛ እና እጅግ መንፈሳዊ አባት ነበሩ።

እግዚአብሔር የአቶ ሰይፉን ነፍስ በአጸደ ገነት ያሳርፍልን!

በጥሞና ስላዳመጣችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።

የአቶ ሰይፉ መታፈሪያ የሥነግጥም መድብሎች እንደታተሙበት ዘመን ቅደም ተከተል፣ ዝርው መጽሐፎቻቸው እና ሌሎች የጥናት እና የምርምር ሥራዎቻቸው ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።

ሀ. የሥነ ግጥም መድብሎች (መጻሕፍት) ዝርዝር

1. 1964 ዓ.ም.፤ ዐፈር ያነሣ ሥጋ። ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ። (154 ገጾች)።

2. 1967 ዓ.ም.፤ የተስፋ እግር ብረት ግጥሞች። ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ። (195 ገጾች)።

3. 1983 ዓ.ም.፤ ውስጠት። አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ። (84 ገጾች)።

4. 1987 ዓ.ም.፤ የተጉዋጎጠ ልብ። ቦሌ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ።

5. 1995 ዓ.ም.፤ ከራስ ድምበር ባሻገር። አትላንታ፣ አሜሪካ። (587 ገጾች)።

6. 2001 ዓ.ም.፤ ዐባይ ፈንጂ የቀበረ ውኀ። ደረኮ አሳታሚ፣ ቦስተን። (608 ገጾች)።

ለ. ዝርው መጻሕፍት

7. 1989 ዓ.ም.፤ ኮልፌ-ሰንዳፋ-ኮልፌ የአዲስ አበባው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀል- ወለድ ትራጀዲ ለታሪክ። የታተመው በዩናይትድ ስቴት ዘአሜሪካ፣ 147 ገጾች።

8. Ha-Hu in America. ለልጆች እና ለወጣቶች ማስተማሪያ የተዘጋጀ መጽሐፍ። አትላንታ፣ ጆርጂያ።

ሐ. ጥናታዊ/ ምርምራዊ መጣጥፎች

1. 1972፤ የባሪያ ስም ባማራው ባህል። Journal of Ethiopian Studies.X,2, ገፅ127-200.

2. 1973, (with Getatchew Haile), “Regional Variations in Amharic: The Dialect of Gojjam”, Journal of Ethiopian Studies. XI, 2, 113-129.

3. 1974, “Sixteen Letters of Ras Mäkonnen and his Sons to Haji Ahmad Aboññ of Harar. Journal of Ethiopian Studies. XII, 2, 179-199.

4. 1978. The Eastern Oromo (K‘ottus) of Ethiopia and Their Time Reckoning “System”, AFRICA. Rivista trimestrale di studi e documentazione dell’Istituto Italo-Africano. Anno # # N. 4, 476-508.

5. 1973 ዓ.ም. [= 1980] “ሥነ/ኪነተቃል በኢትዮጵያ“፣ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል የትውፊት ሴሚናር የቀረበ፣ አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1-3።

6. 1981.“LocalContributiontotheDevelopmentofFolkloristicsinEthiopia”. Addis Ababa University. Department of Ethiopian Languages and Literature. Mimeographed.

7. 1984. “Oral Literature of Ethiopia as Source Material for Children’s Books: A Sample Study”. Rassegna di Pedagogia. I, 2: 45-72.

8. 1986. “Verse-Talk in an Ogaden Front of 1934 Folkloric Study of a Text”. International Conference of Ethiopian Studies, Moscow.

9. 1993. “የፎክሎር መዝገበ ቃላት ጥንቀራ ቅድመ ዝግጅት“፣ Journal of Ethiopian Studies. XXVI, 1, 73-116.

10. 1999 ዓ.ም.፤ “መንገድ ስጡኝ ሰፊ (የገብረ ክርስቶስ ደስታ የግጥም መድብል ግምገማ)”። አንድምታ፣ ቁ.7፣ መጋቢት-ግንቦት፣ ገጽ፣ 4-7።

11. 1999 ዓ.ም.፤ [2017] “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” (ወግ) አንድምታ የሥነጽሑፍ መጽሔት፣ የካቲት፣ ገጽ፣ 1-8።

መ. ወደፊት የሚታተሙ

1. የወዲያው በኩል፤ የግጥም መድብል።

2. ዋዜማ (የግጥም መድብል)

3. TheWork Poetry of the Eastern-Oromos (Qottus) of Ethiopia. Dissertation submitted to in Candidature for the Folklore Department, Institute of African and Asian Studies, University of Khartoum. (Revised and edited in 2019 and ready for publication), ca. 588 pages.

4. በጥንታዊ የግሪክ ሐተታማልክት ላይ የተመሠረተ የትርጕም መጽሐፍ፤ (February 25, 2023) በ ሥነጽሑፍ፣ የሕይወት ታሪክ፣ ጥናትና ምርምር.

————————————————————///————————————————///——————————–

አቶ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው እ. አ. አ November 3, 2022 በአትላንታ፣ ጆርጂያ (አሜሪካ) በ88 ዓመታቸው አርፈው እ. አ. አ November 10,2022 ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል

እግዚአብሔር የአቶ ሰይፉን ነፍስ በአጸደ ገነት ያሳርፍልን! በጥሞና ስላዳመጣችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።

By semenaworq / February 25, 2023
በጌቴ ገላዬ (ዶ/ር)

ኢ-ሜይል፣ [email protected]

የአማርኛ ቋንቋ እና የአፍሪቃ/የኢትዮጵያ ሥነቃል/ፎክሎር መምህር የአፍሪቃ እና ኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል እስያ-አፍሪቃ ጥናት ተቋም፣

ሐምቡርግ፤ ጀርመን

መጋቢት 2015 ዓም።

Copyright © 2026 ሰምና ወርቅ |

19/06/2026

ጸሐፊ፡-ኤልሳቤጥ ወልደ ጊዮርጊስ

ርዕስ፡-Modernist Art in Ethiopia

ገጽ ብዛት፡-xx+339

የታተመበት ዓ.ም.፡- 2019 እ ኤ አ

መጽሐፉ ከመግቢያው ውጪ አምስት ምዕራፎች አሉት።የመጀመሪያው ፤ ከመጀመሪያዎቹ እስከ አጋማሹ የሃያኛው መ/ከ/ዘ ዘበናይነትን የሚገልጽ ነው። ሁለተኛው ምዕራፍ፣ የ1960ቹን ምሑራን ዕሳቤን የሚፈትሽ ነው። ሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ፤ በገብረ ክርስቶስ ደስታ እና እስከንድር ቦጎሲያን እንዲሁም ተማሪዎቻቸው ላይ አተኩሮ ስለ1960ዎቹ ዘበናዊያን የሚያወሳ ነው። አራተኛው ምዕራፍ ደግሞ፣ ከ1967 እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በነበረው በወታደራዊው አስተዳደር ዘመን የነበረውን አርት ያያል፡፡ የመጨረሻው ምዕራፍ፣ እእአ ከ1995 እስክ2015 ድረስ ያለውን ኮንቴምፖራሪ(ወቅታዊ) አርትን የሚመለከት ነው።

አገሪቱ ለዘመናት የቆየ መንፋዊ ሥነ-ጥበብ ታሪከ ቢኖራትም የዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ታሪክ የተጀመረው በ20ኛው መ/ከ/ዘ እንደሆነ ይታወቃል። ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ አጠቃላይ የፖለቲካ፣ ባህል እና ቴክኖሎጂ ውጤት ሆኖ፣ የዘመናይ ኪነ ጥበብ ዕድገት አገራዊ እና አህጉራዊ መልክ መያዙ ሉላዊ ከስተት ነው። ይህ እንቅስቃሴ, በአጠቃላይየሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ እና ጣጣ ላይለመግባት ያለው አቅም እና የተቀባዩ አረዳድ ጥልቀት ውስንነት እንዳለ ሆኖ በሃገሪቱ ሁለንተናዊ ጉዞ ላይ የራሱን አሻራ ማሳረፉ ሊካድ አይችልም። በመሆኑም፣ ሂደቱን እና ተፈጥሮውን ማጥናት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ጥናት ለህትመት መብቃቱን ለዘርፉ በሚኖረው አስተዋፅኦ ብቻ ሳይሆን፤ ከዘርፉጋር በቅርበትም በርቀትም ለሚገናኙ ሙያዎች በእጀጉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መመስከር ይቻላል። የኢትዮጵያ የዝመና እና አዘማኝነት እንቅስቃሴ ከቴክኖሎጂ ያለፈ የዕይታ ኪነ-ጥበብ ሚናን ለመገንዘብ እና የአገራችንን የቅርብ ጊዜ ታሪክ በምልዓት ለመረዳት ያስችላል።

የጥናቱ ፋይዳ

ኤልሳቤጥ በግል ግንኙነቷም ሆነ በሥራ ኃላፊነትዋ አጋጣሚ የጥናቷ አካል የሆኑትንም ሆነ፣ ለጥናቷ የሚጠቅሙ መረጃዎችን ከሚሰጧትን ሰዎች ጋርለመቃረብ ሰፊ ዕድል ያገኘች መሆኗን መልካም ዕድለ ነው። ለእስከንድር ቦጎስያን የነበራትን ቅርበት እና ከእነጸጋዬ ገብረ መድህን ጋር ያላትን ትውውቅ መጥቀስ ይበቃል። ከዚያ ውጪ ለጥናቱ ቃለመጠይቅ ያደረገችላቸው ሰዎች ከፊሎቹ የቅርቧ, ሰዎች ናቸው። ኤልሳቤት የዚህን ጥናት አብዛኛው ምርምር ያደረገችው በኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ሳለች ነው። ከዚያ በኋላም የቪዠዋል እና ፐርፎርሚንግ አርትስ ኮሌጅ ዲንነቷም ሆነ በእስክንድር ቦጎሲያን ኪነጥበብ ማዕከል ዳይሬክተርነቷ ለጥናቱ የሚጠቅሟትን በርካታ ሰዎች ለማግኘት ረድቷታል። በመጀመሪያ "Ethiopian Modernism: A Subaltern Perspective በሚል ርዕስ እአአ 2010 ዓ.ም. በሠራችው ፒኤችዲ ላይተመሥርታ የሠራችው እና ከዚያም በኋላ ወደመጽሐፍ ሲቀየር በአሣታሚው ሥርዓት መሠረት በገምጋሚዎች አስተያየት በመበልፀጉ ቅርፁን ቀይሮ እና ይዘቱ ጎልብቶ የመጣ እና በዚህም ምክንያት ዋጋውን ከፍ ለማድረግ ተቐሏል። ስለዘመናይነት የሚደረገውን በጣም ውስን የሆነ ሃቲት ወደፊት ለመግፋት የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለውም መመስከር ይቻላል። የቃሉን ታሪካዊ እና ፅንሰ-ሐሳባዊ አረዳድ፣ ትርጓሜ እና ትግበራ በሉላዊ አውድ ውስጥ ለማስቀመጥ ዓይነተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

የኢትዮጵያ ጥናት መለወጥ ወይስ ማበልፀግ?

በዚህ ጽሑፍ እኔ የማተኩረው ግን ስለኢትዮጵያ ታሪክበሰጠቸው ግምገማ ብጤ ዕይታዋ ላይ ነው። ሌላውን ትተን ኤልሳቤጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ካነሳቻቸው ጉዳዮች መሀከል በተለይ ሦስት ጉዳዮች ሊጠቀሱ ይገባል። እነርሱም በመቅድሙ ላይ የተገለጹ ናቸው: አንደኛው የኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና የኢትዮጵያ ጥናት ታሪኩ በመረጣ የሚመረት እና ዝም እንዲል የሚደረግ ከፍል እንዳለ የሚወስደው (xii)ዕይታዋ ነው። ይህ አስተያየት አስካሁን የነበረውን የኢትዮጵያ ጥናት ዕውቅና በመንፈግ አፈር ድሜ የሚያስበላ ብቻ ሳይሆን የእርሷ ሥነ-ዘዴ እና ምልከታዋ ሌሎች እውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሰለባ ሲሆኑ፡ እርሷ ያንን አስቀድማ የላቀ ግንዛቤ ኖሯት እራሷን እንደአዳኝ አድርጋ መውሰዷን ያመለክታል። እኔ በቤተመዛግብት የሚቀመጡ ሰነዶች ተመርጠው የሚቀመጡበት ዕድል የለም ለማለት ባልሞከርም፤ ከእነርሱም ቢሆን የሚወሰደው መረጃ የሚገናዘብ፤ የሚፈተሽ እና የሚመዘን መሆኑን ልብ እንዳላለች የሚያሳየኝ ነው ለማለት እደፍራለሁ። ሁለተኛው ደግሞ የእርሷ ጥናት ኖርማቲቭ ፕሮቶታይፕ የሆነውን እና አህጉራዊ ኤጀንሲን ያስወገደ ( reject ያደረገ.) የኢትዮጵያ ነገረሰብ ዕውቀት መረጋጋት ማሳጣት እና በኢትዮጵያ ዘበናዊነት እና ዘበናይ አማራጭ ቴሲስ ለመፍጠር ተስፋ (xiv) ማድረጓ ነው። ሦስተኛው ደግሞ፣ ስማቸውን የጠቀሰቻቸው : አንድ አራት ወጣት እና እየመጡ ያሉ ስል ምሑራን ያለቻቸው ወዳጆቼ የእትዮጵያን አካዳሚክ ፍተሻ አቅጣጫን ያለጥርጥር (xviil) እንደሚቀይሩ ማመኗን መግለጡዋ ነው::

ከመመጻደቅ በመለስ

ሁለተኛው እና ሦስተኛው በተስፋ መልክ የተገለጹ ናቸው። ሁለቱም ግን የኢትዮጵያ ጥናት (ብዙ ቦታ ላይ ማኅበራዊ ሳይንስ እና ነገረ ሰብ ብትልም፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ማተኮሯን እንረዳለን) መቀየርእንዳለበት ከምታመለክትባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ነገር ግን፣ የኢትዮጵያ ጥናት የቱንም ያህል ውሱንነቶች ቢኖሩበትም ኤልሳቤጥ ለጥናቷ በሰጠችው ያልተመጣጠነ ግምት ተመስጣ የማይጠበቅባትን ብቻ ሳይሆን የማትችለውን ኃላፊነት ለራሷ እና ወዳጆቼ ላለቻቸው ሰዎች (በእውነቱ እነዚህ ሰዎች በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ለእኔም ወዳጆቼ ናቸው) መስጠቷን የሚያስመሰከሩ ናቸው። እንዲህ ባታደርግ ስል የምደግፈውን አካሄዷን እያመለከትኩ ነው። ከእርሷ በፊት የተሠሩ ሥራዎችን እንደአስፈላጊነቱ አንስታ ጉድለቱን ማመልከት የአባት ነው። ለምሳሌ፣ የባህሩ ዘውዴን (ፕ/ር) እና የመሳይ ከበደን (ፕ/ር) ከርከር በጨረፍታ በመጠቆም ውሱንነታቸውን መጠቀሟ ተገቢ ነው ((10-12)። እንዲህ ዓይነት ነገሮች የሚታዩት እንደአበልፃጊ(ኮምፕሊመንታሪ) እንጂ እንደምትክ/ቅያሪ አይደለም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ጥናት ተወላገደም፣ ጎበጠም፤ ቀጨጨም፣ ሰነነም የብዙ ዘመናት እና ተመራማሪዎች ድልብ ውጤት ነው። ወደፊትም እየተሞረደ፤ እየተለሰለሰ፣ እየተለበጠ እና እየታሸ ይቀጥላል። የእርሷም ጥናት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል። የእርሷን ዓይነት የለዋጭነት መንፈስ ምን አመጣው ብለን ግን መጠየቃችን አይቀርም። መልሱም ከጸሐፊዋ ታሪክ ብቻ ነው የሚገኘው።

ይኸውም Biographical sketch ባለው ክፍል ነው። በዚያ ውስጥ በወታደራዊው ስርዓት በተፈፀመ ከአገር በመሰደደ ከማንነት ጋር የተያያዘ ለዚህ ፍንጭ የሚሰጠን የፒኤችዲ ድርሳኗ ነው። በዚህ ውስጥ በወታደራዊ ስርዓት በተፈጸመ በደል ከአገር በመሰደድ ከማንነት ጋር በተያያዘ በመነቀል ስሜት ተገድቦ እንደበረዶ በረጋ ትውስታ ሃገር ለቃ የወጣችበትን ሰቆቃዊ ሁኔታ ለሃያ ዓመት በመካድ ከቶኖች በኋላ አለአ በ1995 ወደሃገ መመለሷን ትነግረናለች (it tv)። በመጨረሻም ANA በ2004 ሙሉ ለሙሉ ወደሃገሯ ወስና እስከትመለስ ግን ሦስት ጊዜ ባደረገችው መመላለስ የተገነዘበችው ነገርቢኖር አስተዋፅዖ ልታደርግ እንደምትችል ነው። በዚህ መካከልም ወደሙዚየም ትምህርት ሄደች። ስለዚህም ከባንከርነት ወደኪዩሬተርነት ለመቀየር ቻለች። ለዚህ ፍላጎት መነሻዋም የባህል እና ፖለቲካ ማንነት የተሳሰሩ መሆናቸውን እና በባህል እና ታሪክ ላይ ተዋለሆ የሚያደርግ ተቋም መገንባት ግጭትን የሚያስቀርአወንታዊ ዕድጉት ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ጤናማ የፖለቲካ እና ዕድገት ሂደትን ሊያረጋግጥ ይችላል በሚል እምነት ነው (iv)። ይህ ደግሞ ገንቢ እምነት እና ቁርጠኝነት ነው፡ ከመጣች በኋላ በአስደናቂ ፍጥነት የኢጥምተ ዳይሬከተር ሆነች። ይህንንም በመጽሐፉ መቅድም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አንድርያስ እሸቱ ወደሃገሯ እንድትመጣ እንዳደረገ እና በምሑራዊ አቅሟ ላይ ስለነበራት መታመን የገለጸችው ያረጋግጥልናል። ለነገሩ የእርሱ እምነት ያንን ኃላፊነት መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ለሦስተኛ ዲግሪ ለትምህርት ውጪ ስትላከ ቦታዋ በጥብቅ ተይዞ እስኪጠብቃት የሚያደርስ ነው። ለማንኛውም በጥናቷም ለባህላዊ ተዋስሆ እና ውይይት አስተዋፅአ ያደርጋል ብላ የምታምነው ርዕሰ ጉዳይላይ ሠርታ እርሱንም ለማሳተም ተስፋ ታደርጋለች። በአጠቃላይ፣ ከዚህ ታሪክ ሁለት ነገሮችን እንረዳለን። አንደኛው እራሷ እንደምትለው የዲያስፖሪክ ሁኔታዋ እና አካባቢ የፈጠረባት ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ የእርሷ እሷም በቀድሞ የጥናት ተቋሙ ሰዎች እና በተቋሙ እንዳንድ ሠራተኞች ሳይቀር በነቀፌታ እንድትታይስላደረጋት ወይም እንዲመስላት መሆኑ ይመስላል።

ዲያስፖሪክ ቀውስ

በተለይ የመጀመሪያው ከልከ ያለፈ አህጉራዊ ሁኔታ እና የቅኝ ግዛት ልምድ የታሪኩ አቅጣጫን የሚቃኝ አለመሆኑ የሚያሳስባት አድርጓታል። እንደእርሷ የኢትዮጵያ ገፅታ ከአፍሪካ አሜሪካ፣ የአፍሪካ እና የምዕራብ ኢንድያ ጥናት የቀረፀው የምሑራዊ ፍልስፍና ተጠቃሚ እንዳይሆን ጨቁኖታል ብላ ታምናለች። ስለዚህም የቅኝ ገዢነተ ተስፋፈፊነት፣ እና የበላይነት በአገሪቱ ታሪክ በተለያየ ቅርፅ ቢታይም፣ የእጅ አዙርቅኝ አገዛዝ የዛሬዪቷን ኢትዮጵያ ታሪክ በመቅረፅ ሚና ያለውን ሚና በማኅበራዊ ሳይንስ እና ነገረ ሰብዕ በተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ስም የዘነጋ ነው በማለት ትከሳለች (296)። ለሙጣቷ መሠረቱ ደግሞ "colo niality" ነው፡፡ ምክንያቱም ያለኮሎኒያሊቲ ዘመናዊነት የለምና ነው ነገሩ (4)። "coloniality" ስትል በግርድፉ ቅኝ ተገዢነት ድባብ ማለቷ ነው። ይህ ማለት ደግሞ በዘመናይነት ፕሮጀከት ስም የምዕራብ ሃሳቦች ምዕራባዊ ባልሆነ አውድ ላይ ተረጋግቶ መንሰራፋት ነው። ይህም የምዕራባውያኑ ስርዓት የዓለም ምርጡ ስርዓት ሲሆን፣ ምዕራባዊ ያልሆነው ደግሞ የዚያ አፍራሽ ነውማመን (4) ነው የሚለውን የሰሚር አሜን አሳቤ ታብራራዋለች። በዚህ መሠረት ቅኝ ባትገዛም የኢትዮጵያ ዘመናይነትን የሠራው ይህን ዓይነቱ ድባብ ትርጓሜ እና ልውጠት ነው የሚል ነው (4)። የኢትዮጵያ ጥናት አህጉራዊ መልኩ ስለነት እያከራከርም። የቅኝ ግዛት ድባቡም የአገሪቱን ጥናት መልክ ለመስጠት በሆነ ደረጃ ፋይዳው እያወላዳም። እንደ ካምብሪጅ አፍሪካ ታሪክእና ዩኔስኮ የአፍሪካን ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያን ታሪክለመቀላቀል የተደረገው ጥረት እና በአፍሪካ አውድ ለማየት የተቻለባቸው ጥረቶችን ማስታወስ ያስፈልጋል። ለምሳሌ የዩኔስኮ ጀነራል ታሪከም የኢትዮጵያን ሁኔታ የተመለከበት መንገድ ፈፅሞ ኢትዮጵያ ታሪክበተነጣይ ትርክት ዕሳቤ አይደለም። የቅኝ ግዛቱ ትማልን በአሸናፊነት ብትወጣም የውስጥ ሁኔታውን ከላይቤሪያ ሁኔታ ጋር በማነፃፀር ትረካው ሳያስቸግረው ለማሳየት የቻለ ነው። በተቀረ ግን የኢትዮጵያን ጥናት ፈፅሞ በአፍሪካ ዕይታ ማዕቀፍ ሙሉ ለሙሉ መግጠም ግን አይቻልም። ለዚህ ነው ኤልሳቤጥ የኢትዮጵያ ጥናት ዘለለው; ዘነጋው) አስወገደው ግድ የለሽ ሆነበት (ምክንያቱም የተለያዩ ቃላትን ትጠቀማለች ለምሳሌ ignore/ omit/ reject/disregard) ۲۶۰۰۸ (colo-nial domination, colonial exploitation) የቅኝ ግዛት ልምድ እና የቅኝ ግዛት ነገረ ዕውቀት (co-lonial episteme) ስስነት ለምን እንዲህ ምርር ምርርእንደሚያደርጋት ጥያቄ ማንሳት የሚገባን። ሩቅ ሳንሄድም በዚህ መጽሐፍ በአፍሪካ የቅኝ ግዛት ታሪከ እና በኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ታሪክ መካከል ያለውን ውጥረት እና ያልተፈታ ግንኙነት ምፀት እንደምታይ እና ሃልዮት እንደምትቀርፅለት ያደረገችውን ተስፋ (15) እንኳን የቋንቋ ጫወታ ካልሆነ በስተቀር ለማድረግ እንዳልቻለች ዋቤ አድርገን መተቸት የምንችለው። መረዳት ያለብን የኢትዮጵያ ጥናት ከቅኝ ግዛት አንፃር ሲታይ ያለውን ድባብ መፈተሸ፣ መተንተን እና ማብራራት ያስፈልጋል። ነገር ግን የቅኝ ግዛት ስሜት እና ድባብ የኢትዮጵያ ጥናትንን እንዲደርዝ መጠበቅ የለበትም። ኢትዮጵያን በአፍሪካ አውድ ለማየት መሞከርም አዲስ ነገርሳይሆን፣ ኤልሳቤጥ ከምትጠቅሰው ከፍቅሩ ነጋሽ ጥረት በተጨማሪ እንደውም አስቀድሞ ተሻለ ጥበቡ (ፕ/ር) ብዙ እንደሰራበት ማንሳትም ያስፈልጋል። ለምሳሌ፣ የአትዮጵያ ጥናት ከአፍሪካ ድባብ መነጠሉን ለመሞገት ጥረት ያደረገበትን ለኢትዮጵያ የሚሰጡ የተለያዩ ገፅታዎችን በማንሳት የተአበትን "Ethiopia: The "Anomaly" and "Paradox" of Africa" በሚል ርዕስ የጻፈውን መጣጥፍ መጥቀስ ይበቃል። የሄግልን የታሪክአረዳድ ፍልስፍና ሳይቀር የሚተችበት መጽሐፉ ጉዳዩን በስፋት የሚያነሳበት ነው።

ሁለተኛውን ጉዳይ በስሱ ጠቅሼ ልቋጭ። በመጽሐፉ በአወንታዊ መልኩ ከተጠቀሱ "ተመራጭ" ሰዎች እና ሥራቸው ተነስተን በኢትዮጵያ ጥናት አቅጣጫ መዘውር ላይ ያላትን አቋም ስናዳብልበት፤ ኤልሳቤጥ ደጋግማ በፆታ ሽፋን ውስጥ ብትደበቅም በአንጋፋ የኢትዮጵያ ጥናት ሰዎች ላይ ያላትን ቅሬታ፣ በጥናቱ ራሱ ላይሳታውቀው ቂም ያሳደረች ያስመስላታል። ጥናት ከስደተኛነት እና መጻጉዕነት መንፈስ በተላቀቀ ዕሳቤ ቢታይ ዕይታውን ሊያቃና እንደሚችል እያስታወስኩ፣ ከዚያ በመለስ ሥራው ያለውን አስተዋፅኦ በድጋሚ እመሰክራለሁ። አንድ ነገር ለመጨመር ከአንድርያስ ዲያስፖራ አስተዳደር ሹመቷ ካተረፍነው፣ በዚህ መጽሐፍ ያተረፍነው ይበልጥ ይሆን ብል ማጋነን ይሆን?

ዳሰሳ አቅራቢ : ብርሃኑ ደቦጭ ፍትሕ መጽሔት ቅፅ 02 ቁጥር 70 የካቲት 2012

19/06/2026

ርእስ፡- “የትሩፋን ናፍቆት”
ጸሐፊ፡- ሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን
አሳታሚ፡- ሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን
የታተመበት ዓመት፡- 2006 ዓ.ም.
ገጽ፡-264
ዋጋ፡- 55.00 ብር

መግቢያ

ይህ ግምገማ በሦስት ክፍሎች የሚከፈል ሲሆን፣ የመጀመሪያው ክፍል መጣጥፎችን ለመገምገም እንደ ሐሳብ ማዕቀፍ የሚያገለግሉንን ጥያቄዎች የሚያስተዋውቅ ነው። በሁለተኛው ክፍል በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ በመመሥረት “በትሩፋን ናፍቆት” ውስጥ የተሰባሰቡትን መጣጥፎች የሚመለከት ሲሆን፣ በመጨረሻም መደምደሚያ ይሆናል።

1. የግምገማው የሐሳብ ማዕቀፍ
በትሩፋን ናፍቆት ውስጥ የተካተቱትን መጣጥፎች ጸሐፊው ከቀረጸለን ዓለም (narra ve world) አንጻር ለመረዳት የሚያግዙ ሦስት ሥነ ጹሑፋዊ ጥያቄዎች ለዚህ ግምገማ ማዕቀፍ ሆነው ያገለግሉናል።

ሀ. የመጀመሪያውጥያቄጸሐፊውመጣጥፎችንለመጻፍ የተነሣበት መነሻ፣ መድብሉ ተደራሽ ሊያደርገው የፈለገው አካል፣ ጸሐፊው የሚያነሣቸውን ጉዳዮች የሚያይበትን ዕይታ ለማየት ይሞክራል፤

ለ. ሁለተኛው ጥያቄ የመጣጥፎቹን ይዘት እና የሚያነሡት የመከራከርያ ነጥቦች ላይ ያጠነጥናል፤

ሐ. ሦስተኛው እና የመጨረሻው ጥያቄ ጸሐፊው ሐሳቡን ለማጐልበት የተጠቀመባቸውን የቋንቋ እና ሥነ ጹሑፋዊ ሥልቶች እንዲሁም የመጽሐፉን መዋቅር እና የሐሳብ ፍሰት ይፈትሻል።

2. ግምገማ
ሀ. “የትሩፋን ናፍቆት” ከጸሐፊው ዓላማ፣ ዕይታ እና ተደራሽ ከአደርገው አካል አኳያ

ጸሐፊው “መሿለኪያ” ብሎ በሰየመው መግቢያ ላይ በመድብሉ ውስጥ የተካተቱት ጽሑፎች የተጻፉበት ዋነኛ መንሥኤ “ክርስቶስን ከማክበር፣ መንግሥቱን ከመናፈቅና እናንተን ውዶቹን ከመውደድ ውስጥ የተመዘዘ” እንደ ሆነ ይነግረናል። ከእዚህም በመነሣት የዚህ መድብል ተደራሽ ክፍል በክርስቶስ ቤተ ሰብ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች እንደሆኑ እንረዳለን። ይህን ዕሳቤ የሚያጠነክረውም ጸሐፊው “ትሩፋን” የሚለውን እና በመጽሐፉ ርእስ ውስጥ የተጠቀመበትን ቃል ዐውዳዊ አፈታት ሲያቀርብ “ቅሬቶች፣ እምነታቸው የጸና፣ ምግባራቸው የቀና፣ ከብዙኀኑ በተለየ መንገድ ለኪዳኑ ታማኝ በመኾን የሚጸኑ” እንደ ሆኑ ትርጓሜ ይሰጣል። በእነዚህ መጣጥፎች ውስጥ ግልጽ የሚሆንልን አንድ እውነታ በጸሐፊው ዕይታ ትሩፋን አንድን ቤተ እምነት ወይም የሃይማኖት ጐራ የሚወከሉ ሳይሆኑ የእግዚአብሔርን ቃል የተጠሙ፣ የክርስትናን ህዳሴ የሚመኙ፣ በማንኛውም ክርስቲያናዊ ቤተ እምነት ታዛ ሥር የሚገኙ ግለ ሰቦች መሆናቸውን ነው። ከዚህም የተነሣ ጸሐፊው በተለያዩ መጣጥፎች ውስጥ በሚነሡ ጉዳዮች ላይ ከኦርቶዶክሳዊውም ሆነ ከወንጌላዊው ዐውድ ያስተዋላቸውን እክሎች መሳ ለመሳ ያቀርብልናል። ይህ የመጣጥፎቹ ጠንካራ ጐን ብዬ ከምፈርጃቸው አበረታችና ይበል የሚያሰኙ ገጽታዎች አንዱ ነው።

እዛው መግቢያው ላይ ጸሐፊው ይህን መድብል ሲያዘጋጅ ዓላማው “ራሳችንን ዐይተን ለመታዘብ፣ ከጉድለታችን ለመታረም እንጐተጐት” (ገጽ 17) ዘንድ እንደ ሆነ ይነግረናል። ከዚህም በመነሣት በመጣጥፎቹ ውስጥ የተካተተው ማኅበረ ሰባዊ ሂስ የቀረበበት ዕይታ ገለልተኛ ከሆነ እና ከማኅብረ ሰቡ ውጭ ሆኖ ነገሮችን የሚያጠና (e c) ሳይሆን፣ የማኅበረ ሰቡ አካል በሆነ እና ከማኅበረ ሰቡ ዕቅፍ ውስጥ ምልካታውን የሚያካፍል (emic) እንደሆነ ለመረዳት እንችላልን። ይህ አመለካከትም በተለያየ መልኩ ተንጸባርቆ ይገኛል። ከሁሉም “እኛ” የሚለው ድምፅ ጉልሕ እንደ መሆኑ ጸሐፊው ከታዘባቸው እክሎች ራሱን ንጹሕ ለማድረግ እንዳልሞከረ ስለሚያመላክት መፍትሔውም በእኛ እጅ እንዳለ ሲጠቁመንም ለመቀበል አያዳግተንም። በርግጥ የተወሰነ ገለልተኝነት መፍጠር ካልተቻለ በአንድ ማኅበረ ሰብ ውስጥ ሆኖ ሂስን ማቅረብ የዕይታ መጥበብን ሊያስከትል ይችላል።

በተለያዩ መጣጥፎች ውስጥ ተንጸባርቀው የምናስተውላቸው የጸሐፊው ጠንካራ ስሜቶች የሚመነጩትም ከዚሁ ዕይታ እንደ ሆነ መገመት ይቻላል። ለምሳሌም ያህል “ባለቤት የናቀው አሞሌ” በተሰኘው ጽሑፍ ውስጥ በአንድ ወቅት ተነሥተው የነበሩ የተሓድሶ እንቅስቃሴዎች ያጋጠማቸውን እክል በማውሳት ጸሐፊው የራሱን እማኝነት የሚያካፍልበት ክፍል ማውሳት ይቻላል (ገጽ 37)።

በተወሰነ መንገድ በጽሑፎቹ ውስጥ የምናየው ጥልቅ ስሜት ጸሐፊው ላነሣቸው ጉዳዩች የሰጠውን ጉልሕ ስፍራ እንድንረዳ ብቻ ሳይሆን፣ እኛ አንባቢዎች ጽሑፎቹን እንደ ቀዝቃዛ ማኅብረ ሰባዊ ሂሶች ወይም ትንታኔዎች ብቻ እንዳናነባቸው ያደርገናል። ሆኖም ግን በአንዳንድ ስፍራ ይሄ ጠንካራ ስሜት የምሬት ወይም የፍረጃ ቃና ሲይዝ እናስተውላለን። ጸሐፊው ከሚያነሣቸውም ምሳሌዎች (ለምሳሌ ገጽ 208 – 13) ጀርባ ያለው ሃቅ ባያጠራጥርም ምናልባትም አብዛኞቹ የአንድ ማኅበረ ሰብ እክል ሳይሆኑ መንሥኤው የሰው

ዘር የጋራ ሊባሉ የሚችሉ ችግሮች ከመሆናቸው አንጻር የጸሐፊው ምልከታ ጥልቅ ቁጣ እና ትዝብት የፈጠረው ምሬት ውጤት ይሆን ብለን እንድናስብ ያደርገናል።

ሁንም ከመሿለኪያው ሳንወጣ ጸሐፊው በማያሻማ መልኩ መጣጥፎቹ ያዘሉት ሂስ ያነጣጠረበትን ማኅበረ ሰብ “ድሪቶ በለበሰ … ክፋት ኅሊናን በሚኮሰኩስበት ዘመን” ውስጥ መገኘቱን ከዚህም በመነሣት መፍትሔዎች በመፈለግ ሂደት ውስጥ የበኩሉን ሊያበረክት እንዳለ ይናገራል። በዚህም ረገድ ጸሐፊው ልንሄድባቸው የሚገቡንን መንገዶች ይጠቁመናል፤ ይህንንም የሚያጠነክሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ሌሎች ማስረጃዎችን ያቀርብልናል እንጂ፣ ‘እኔ የያዝኩት መፍትሔ ፍቱን መድኃኒት ነውና ያለማቅማማት ተጋቱት’ ብሎ አይሰብከንም። ይህም ጸሐፊው ለአንባቢው ያለውን ክብር እንዲሁም ደግሞ ያነሣቸው ጉዳዮችን ውስብስብነት መረዳቱን ያሳየናል።

ለ. “የትሩፋን ናፍቆት” ከጽሑፎቹ ይዘት እና መከራከርያ ነጥቦች አኳያ

ምንም እንኳን በ“ትሩፋን ናፍቆት” በተካተቱ መጣጥፎች ውስጥ አያሌ ጉዳዮች ቢነሡም በእኔ ዕይታ እነዚህ ጉዳዮች በሦስት ዋነኛ ጭብጦች ዙሪያ ያጠነጥናሉ። እነዚህም ቤተ ክርስቲያናዊ ተሓድሶ፣ ግለሰባዊ ተሓድሶ እና ብሔራዊ ተሓድሶ ናቸው።

ቤተ ክርስቲያናዊ ተሓድሶ፡- ቤተ ክርስቲያን በሞራላዊ እና መንፈሳዊ ተሓድሶ አልፋ በኅበብረተ ሰቡ ውስጥ በሚጠበቅባት ሥፍራ ላይ መቀመጧ የመጀመሪያው “የትሩፋን ናፍቆት” ነው ብንል የምንሳሳት አይመስለኝም። በአንባቢ ልብ ውስጥ ምኞትን የሚያጭሩ፣ የተሻለ ክርስቲያናዊ ተሞክሮን ከአድማስ ባሻገር እንድናይ እና ያን ናፍቆት እንድንጋራ የማድረግ ኀይል ያላቸው ትዝብቶችን ከምናስተውልባቸው መጣጥፎች መካከል “ስሙን መልሱልን” እና “ማፍረስም መሥራት ነው” በዐበይትነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ቤተ ክርስቲያናዊ ተሓድሶን በተመለከተ ጸሐፊው በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ እና በሌሎች ሥፍራዎች ላይ የሰነዘራቸው ትችቶች የኢትዮጵያ ክርስትና እዚያም ቤት እዚህም ቤት የደረሰበትን መንታ መንገድ የሚያመለከቱ እና አስፈላጊ የሆነ የተሓድሶ መሥመሮችንም በሰከነ መልክ በመጠቆም የትሩፋንን ድርሻ የሚያመላክቱ ናቸው።

ግለ ሰባዊ ተሓድሶ፡- በትሩፋን ናፍቆት ውስጥ የምናገኛው ሁለተኛ መሪ ጭብጥ ግለ ሰባዊ ተሓድሶ ነው። “እንከራከር ወይስ ́እንጋደል ́?”፣ “የበርናባስ ብፅዕናዎች”፣ “መንገዱም ቢጠብ፣ ጠብን እንጠብ”፣ “ሕልም አንሸጥም” የተሰኙት መጣጥፎች በተለያየ መንገድ እያንዳንዳችን ወደ ራሳችን መለስ ብለን ነገሮችን እንድንቃኝ የሚጋብዙ ናቸው።

በተለይም ደግሞ “ቢዘገይም አይዘገይም” የተሰኘው መጣጥፍ ትንቢተ ዕንባቆም ላይ የተመረኮዘ ክሽን ያለ አብራሪ ስብከት (expository preaching) ላይ በመመሥረት የእግዚአብሔር ሰው፣ በዙሪያ በሚመለከተው ነገር ግራ እንደማይጋባ፣ ይልቁንም ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ በማድመጥ እና በማምለክ ተሓድሶ እንደሚያገኝ ይነግረናል (ገጽ 75)። ከመጽሐፉ አጠቃላይ ዐውድም እንዲህ ያለው ሰው የዘመኑን ግራ መጋባት ከእግዚአብሔር ልዕልና እና ግርማ አኳያ በማየት በእምነት እግዚአብሔርን ከሚጠባበቁት ትሩፋን ወገን ይሆናል።

ብሔራዊ ተሓድሶ፡- “ሴት ምናችን ናት” እና “በስሜት ስንከንፍ እውነትን እንዳንገድፍ” የተሰኙት መጣጥፎች ቀጥተኛ ማኅበረ ሰባዊ ትችቶች ሲሆኑ፣ ብሔራዊ ተሓድሶ (እዚህ ጋር በደፈናው የግብረገብ ነገር እንጂ መንፈሳዊውን ብቻ አያመለክትም) ያልነውን ጭብጥ ምሳሌ ሆነው ያገለግላሉ። ጸሐፊው ሥር ሰደድ ማኅበረ ሰባዊ እክል የሆነውን በሴቶች ላይ የሚደርስ አካላዊ ጥቃትን እንደ መነሻ በመያዝ በማኅበረ ሰባችን ውስጥ ስለ ሴቶች ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን እንዲሁም ደግሞ በእነርሱ ላይ የሚደርሱ በደሎችን በማውሳት ሞራላዊም ሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊም ትችት ይሰጠናል። እንዲሁም ደግሞ “በስሜት ስንከንፍ እውነትን እንዳንገድፍ” በሚለው ጽሑፍ ውስጥ ሚዛናዊነት ስለ ጐደለው ቲፎዞነት ይወቅሰናል። እነዚህ ሁለት ጽሑፎች ላነሷቸው ሐሳቦች በሚመጥን፣ ቅልብጭ እና ጥርት ባለ የሐሳብ ፍሰት የመከራከሪያ ነጥባቸውን ያቀርባሉ። በተጨማሪም፣ ጸሐፊው ከቤተ ክርስቲያን ዐውድ ውጭም ሰፊውን ማኅብረ ሰብ ያማካሉ ጉዳዮች ላይ ያለውን የበሰለ ዕይታ በጨረፍታ እንድናይ ያደርገናል።

ከዚህ በዘለለ፣ ብሔራዊ ተሓድሶ ብለን ከፈረጅነው ጭብጥ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የሚመስሉ ሐሳቦች “ባለቤት የናቀው አሞሌ”፣ “እንከራከር ወይስ ‘እንጋደል’?” እና “የኔን መልክ ያያችሁ” በሚሉት መጣጥፎች ውስጥ እናገኛለን። ምንም እንኳን የተነሡት ትችቶች ተገቢ እና በተወሰነ መልክ አገራዊ ውይይቶች ላይ ያሉ ሐሳቦችን የሚያስቀጥሉ ቢሆንም ጸሐፊው ተደራሼ ብሎ ከያዘው ማኅበረ ሰብ እና ለጽሑፎቹም ከያዘላቸው ዋነኛ ዓላማ ውስኑነት የተነሣ ሊነኩት የሞከሩትን ይህን ጭብጥ በወጉ መሸከም የከበዳቸው ይመስላሉ። ለምሳሌም ያህል፣ “ባለቤት የናቀው አሞሌ” ያነሣው የባህል እና የማንነት ቅየጣ ጉዳይ ከዕለት ወደ ዕለት አሳሳቢነቱ እያየለ የመጣ ብሔራዊ ችግር እንደ ሆነ አያጠራጥርም። ጸሐፊው ምናልባትም ይህን

አገራዊ ጉዳይ ከክርስትና ዕይታ አንጻር ሊያየው ሞክሮ እንደ ሆነ ክርስትና የኢትዮጵያ የባህልና የትውፊት አካል ከመሆኑም በላይ ቤተ ክርስቲያንም በብሔራዊ ታሪክ ላይ በጐም ክፉም አሻራዎቿን እንደማኖሯ ይበል የሚያሰኝ ነው። ሆኖም ግን በአንዳንድ ስፍራ ላይ አገራዊ የሆነውን ጉዳይ ቤተ ክርስቲያናዊ በሆኑ ማስረጃዎች ለመደገፍ ሙከራ አድርጓል። ይህ ደግሞ ምሳሌዎቹ (ገጽ 33፡ 43፡ 44) የብሔራዊውን ጉዳይ ለማሳየት አቅም እንዲያንሳቸው ምክንያት ሆኗል። ይህ በመሆኑም የነገረ ሐሳቡን ጠንካራ ጎን የሚገባውን ያህል እንዳናስተውል እክል ፈጥሯል።

3. “የትሩፋን ናፍቆት” ከቋንቋ፣ መዋቅር፣ እና ሐሳብ ፍሰት አኳያ
“የትሩፋን ናፍቆት” እየተረሱ የመጡ እና በአንዳንዶቻችን ዘንድ ፍጹም የማይታወቁ ቃላትን ማስታወስ እና ማስተዋወቁ አስደሳች ቢሆንም፣ ከመጽሐፉ ተደራሽ አካል አንጻር በአንዳንድ ሥፍራዎች ላይ ቀላል እና በሰፊው የተለመዱ ቃላት ሊያገለግሉ ሲችሉ ከበድ ያሉ እና በተወሰነ ጠባብ ዐውድ ውስጥ የተለመዱ ቃላት በጥቅም ላይ መዋላቸው ለአንባቢ ሊያዳግት ይችላል። ብሎም መጣጥፎቹ ወቅታዊ እና ማኅበረ ሰባዊ ጉዳዮችን ለሰፊው አንባብያን ለማድረስ፣ መፍትሔም ለመጠቆም የታቀዱ እንጂ ምሁራዊ ውይይት ወይም ጥናት አለመሆናቸው ቋንቋውን ለመረዳት ቀለል ያለ ቢሆን ኖሮ ተመራጭ ያደርገው ነበር።

“የትሩፋን ናፍቆት” ጠንካራ ጐን ተብሎ ሊወሳ ከሚገባቸው ነገሮች መካል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በጥቅም ላይ የዋሉበት ውበት ነው። ጸሐፊው የጽሑፉን ፍሰት ላለመረበሽ ከወሰደው ጥንቃቄ ባሻገር ጥቅሶች

ከሞላ በጐደል በትክክለኛ ስፍራ በተገቢ ሁኔታ ይህ ቀረህ በማይባል የአፈታት ብቃት ቀርበዋል። ይበልጡንም ደግሞ በአብዛኞቹ መጣጥፎች ውስጥ (በተለይም “ቢዘገይም አይዘገይም” እና “የበርናባስ ብፅዕናዎች”) የምናገኘው አብራሪ ስብከት አንባቢው ቃሉን በሕይወቱ መተግበር እንዲያስችለው የሚያግዝ ምክር ወይም ተዛምዶ አክሎ ማቅረቡ የጽሑፎቹን ጠቃሚነት እና ጥራት ከፍ ያደርጋል።

ጸሐፊው ከመጽሐፍ ቅዱስ ለጥቆም ምሳሌያዊ ትረካዎችን፣ ግለ ታሪኮችንና አባበሎችን እንዲሁም ከተለያዩ ምንጮች የተወሰዱ ምሳሌዎች እና ማብራሪያዎች በመጠቀም ጽሑፉን ያበረታል። ከእዚህ ጋር በተያያዘ ልንጠቅሰው የሚገባን በአንዳንድ ሥፍራዎች ላይ የቀረቡ ማብራሪያዎች ምንም ያህል ቁም ነገር ቢያዝሉ ወይም አስተማሪ ቢሆኑም የሐሳቡን ፍሰት የሚያቋርጡ እና ከጽሑፉ ጭብጥ ለማፈንገጥ የሚታገሉ በመሆናቸው በግርጌ ማስታወሻ ላይ፣ አልያም ለብቻ እንደ ተጨማሪ ማብራሪያ ቢቀርቡ ተመራጭ ይሆን ነበር።

ከቅርጽ እና የሐሳብ ፍሰት ጋር በተያያዘ የዐረፍተ ነገሮችን ጉዳይ ማንሣት ግድ ይሆንብናል። ይህን መድብል በዘፈቀደ በማንኛውም ገጽ ላይ ብንከፍተው ከአንድ በላይ የሚሆኑና ዐራት መሥመሮችና ከእዚያ በላይ ርዝመት ያላቸው ዐረፍተ ነገሮችን ማግኘታችን አየቀሬ ነው። አንዳንድ ስፍራ ላይ አንድ ዐረፍተ ነገር አንድ አንቀጽ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ የአንባቢን መረዳት የሚገዳደር እና ጸሐፊው ያነሣውን ነጥብ ለመረዳት የሚያዳግት ስለሆነ ከጽሑፎቹ ደካማ ጐኖች ይመደባል።

በመጨረሻም፣ “የትሩፋን ናፍቆት” የግርጌ ማስታወሻ እና የዋቢ መጽሐፍት አጠቃቀም እና አቀራረብ ማመስገን ግድ ይላል። ብሎም ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ጸጋዬ ገ/መድኅን፣ ጌታቸው ኃይሌ፣ ከበደ ሚካኤል የመሳሰሉ አያሌ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በአግባብ ጥቅም ላይ ውለው እና በዋቢ መጽሐፍት ዝርዝር ላይ በጉልሕ ተቀምጠው መገኘታቸው አስደሳች ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ጥናትም በር ከፋች ነው።

መደምደሚያ

በእዚህ ግምገማ ለማሳየት እንደሞከርሁት “የትሩፋን ናፍቆት” የመጣጥፎች መድብል ጸሐፊው በምድራችን ቤተ ክርስቲያናዊ፣ ግለ ሰባዊ እና ብሔራዊ ተሓድሶ አስፈላጊ እንዲሆን ያደረጉትን ማኅብረ ሰባዊ ሕጸጾች ያሳየናል። የእግዚአብሔርን ቃል፣ እማኝ ታሪክን፣ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ አስተሳሰብን ግብዓት አድርጐ ለእነዚህ እክሎች መፍትሔ ያለውንም መንገድም ይጠቁመናል። ከእዚህም በመነሣት ምንም እንኳን በየትኛውም መጣጥፉ ላይ በግልጽ ባይሰፍርልንም “የትሩፋን ናፍቆት” ሁሉን አቀፍ ተሓድሶ ናፋቂ እንደ ሆነ መገመት እንችላለን።

Reviewer : Meron Teklebirhan, Originally posted on Hintset Christian society's Website

18/06/2026

ርእስ:- መጽሐፍ ቅዱስና የትርጓሜ ስልቱ:- ቅዱሳት መጻሕፍት እንዴት ይነበቡ? እንዴት ይተርጐሙ? እንዴት ይተግበሩ?
ጸሐፊ:- ምኒልክ አስፋው
የታተመበት ቀን:- 2009 ዓ.ም.
የታተመበት አገር:- ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ
የገጽ ብዛት:- 457

መግቢያ

መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቲያኖች ዘንድ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተደርጎ የሚወሰድ ጥንታዊ ሰነድ ነው። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ይኸው መጽሐፍ እየተነበበና እየተተረጐመ እስከ አሁን ዘልቋል። ታዲያ፣ ‘መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ሰነድ ስለ ሆነ እንዴት እናንብበው? እንዴትስ ከሕይወታችን ጋር እናዛምደው?’ የሚሉ ጥያቄዎች ሁል ጊዜ የሚነሡ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን እና አሁን እኛ ባለንበት ዘመን መካከል ያሉ የባህል፣ የታሪክ፣ የማኅበራዊ ሕይወትና ሌሎችም ልዩነቶች መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብብ በጥንቃቄ እንጂ በዘፈቀደ መሆን እንዴለለበት የሚጠቁሙን ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ሰነድ ስለ ሆነ በተጻፈበትና በእኛ ዘመን መካከል የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክና የሥነ ጽሑፍ ሰፊ ልዩነት አለ። ከዚህም የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስን ተገቢ በሆነ መልኩ ለመረዳት እነዚህን ክፍተቶች ማጥበብ ይኖርብናል፤ ይህ ደግሞ ሥነ አፈታትን አስፈላጊነት የግድ ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ከእኛ ሕይወት ጋር ከማዛመዳችን በፊት፣ በተጻፈበት ዐውድ ውስጥ መረዳት አለብን፤ ይህም ማለት መጽሐፍ ቅዱስ ለቀዳማይ ተደራሲያኑ ያልተናገረውን ለእኛ አይናገርም እንደ ማለት ነው። ለዚህ ነው የመጽሐፍ ቅዱስ አጥኚዎችና አንባቢያን ለመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊና ሥነ ጽሑፋዊ ዐውድ ትልቅ ትኩረት የሚሰጡት።

ምኒልክ በዚህ ሥራው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ኀላፊነት ባለው መንገድ እንዴት ማንበብና ከዕለት ተ’ለት ሕይወታችን ጋር ማዛመድ እንዳለብ ያስረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብቡ/የሚያጠኑ ሰዎች የተለያዩ የአፈታት ዘዴዎችን እንደሚከተሉ ይታወቃል። ምኒልክ መጽሐፍ ቅዱስን ሥነ ጽሑፋዊ እንዲሁም ታሪካዊ ዐውዱን ባገናዘበ መልኩ እንዴት ማንበብ እንዳለብን ከማሳየቱም በላይ፣ “ክርስቶስን ያማከለ” መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጓሜ (Christocentric hermeneutics) ወደ ትክክለኛው አምላካዊ ሐሳብ ለመድረስ ያጋዛል የሚል ብርቱ ሙግት ያቀርባል (ገጽ 14-15)።

የመጽሐፉ አወቃቀር

መግቢያና መደምደሚያን ሳይጨምር መጽሐፉ በስድስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው። የመጀመሪያው ምዕራፍ ስለ መጽሐፍ ቅዱስና ስለ ትርጓሜ አስፈላጊነት የሚያብራራ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ባሕርይም ሆነ የተጻፈበት ዘመን የትርጓሜን አስፈላጊነት ያሳያሉ። መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊና ሰብአዊ ባሕርያት ያሉት መጽሐፍ ነው። መለኮታዊናቱ በእግዚአብሔር መንፈስ ምሪት መጻፉ ሲሆን፣ ሰብአዊ ባሕርይው ደግሞ በሰው ልጆች ቋንቋ እና በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ መጻፉ ነው። ይህ በመሆኑም ምክንያት የቋንቋ ሕግጋትን ባገናዘበ መልኩ መፍታት እንደሚያስፈልግ በዚህ ምዕራፍ ተብራርቷል።

ሁለተኛው ምዕራፍ ስለ መጽሐፍ ቅዱስና መገለጥ ትንተና የቀረበበት ነው። እግዚአብሔር በተለያዩ መንገዶች ራሱን የገለጠ ሲሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን ከገለጠባቸው መንገዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው። በዚሁ ክፍል ውስጥ ከመገለጥ በተጨማሪ ቀኖና (canon) ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው። ‘መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ ስንት መጻሕፍትን ይዟል?’ የሚለው ጉዳይ የተለያዩ ቤተ እምነቶች የሚለያዩበት ነው። ልዩነቱን መገንዘብ እንችል ዘንድ በኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክና ፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ስላሉ የቀኖና ልዩነቶች ሰፋ ያለን ትንታኔ አቅርቧል።

ሦስተኛው ምዕራፍ የትርጓሜ ሥልቶች የተዳሰሱበት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከትውፊት ጋር ያለው ተዛምዶ፣ የአይሁድ የትርጓሜ ስልት፣ የቤተ ክርስቲያን አበው ትርጓሜ ስልቶች ሰፊ ትንታኔ አግኝተዋል። ከቤተ ክርስቲያን አበው መካከል እንደ ፖሊካርጶስ፣ ቀሌምንጦስ፣ አግናጤዎስ፣ አርጌንስ፣ ዮሐንስ አፈወርቅና ቅዱስ አውግስጢኖስ ያሉት የትርጓሜ ሥልቶች ለማሳያነት ቀርበዋል። በዚሁ ክፍል ሌላው ትልቅ የሆነ ትኩረት የተሰጠው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትርጓሜ ሥልት/ባህል (የአንድምታ ትርጓሜ) ነው። የአንድምታ ታሪካዊ አመጣጥና የሥነ አፈታት መንገድ በስፋት የተብራራ ሲሆን፣ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በመውሰድ አንደምታው እነዚህን ክፍሎች እንዴት እንደሚፈታቸው በምሳሌነት ቀርበዋል። በታሪክ ውስጥ የነበሩና አሁንም ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያን ሁል ጊዜ አንድ ዐይነት የአነባበብ መንገድ አይከተሉም፤ ስለዚህም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያን መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እንደተረዱት መገንዘብ የእኛን አነባበብ በመቅረጽ ገረድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ምዕራፍ አራትና አምስት የመጽሐፉ ወሳኝ ክፍሎች ናቸው። በእነዚህ ሁለት ምዕራፎ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሥነ ጽሑፋዊ ቅርጽን (literary genres) ባገናዘበ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት መፍታች እንደሚቻል የሚያሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ሥነ ጽሑፋዊ ቅርጽ ወይም ዘውግን የያዙ መጻሕፍት ስብስብ ነው። “ልክ ሰዎች የየራሳቸው መልክና ገጽ እንዳላቸው ሁሉ፣ ጽሑፍም የራሱ መልክና ገጽ ወይም ጾታ አለው።” (ገጽ 151)። በዚህም መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሕግ፣ የታሪክ፣ የትንቢት፣ የግጥም፣ የቅኔ፣ የደብዳቤ፣ የአቡቀለምሲስ (ራእይ) የመሳሰሉ ሥነ ጽሑፋዊ ቅርጾችን እናገኛለን።

በምዕራፍ አራት ውስጥ ለኦሪት መጻሕፍት፣ ለታሪክ/ትረካ መጻሕፍት፣ የጥበብ/ቅኔ እንዲሁም የትንቢት መጻሕፍት የተለየ ትኩረት ተሰጥቷል። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን እያንዳንዱን የሥነ ጽሑፍ ቅርጾች ባሕርይ በማብራራት ተገቢ የሆኑ የአነባበብ መንገዶችን (ትርጓሜያዊ ሥልቶችን) ይጠቁማል። ክፍሉ ንድፈ ሐሳብን ወይም መርሖዎችን ብቻ የሚዘረዝር ሳይሆን፣ ተግባራዊ የሆኑ ምሳሌዎችንም ያካተተ ነው።

ምዕራፍ አምስት ትኩረቱ የአዲስ ኪዳን መጻሓፍት ላይ ነው። በአዲስ ኪዳን የሚገኙ የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ቅርጾች እንዴት መፈታት አለባቸው የሚለውን ከማሳየቱ በፊት፣ መጽሐፉ አዲስ ኪዳንን ለመረዳት ወሳኝ የሆኑ ታሪካዊ ዳራዎችን ያሳያል። በዚህም ክፍል ይሁዲነት፣ የይሁድ የሃይማኖትና የፖለቲካ ቡድኖች ተዳስሰዋል። በመቀጠል ወንጌል፣ መልእክቶችና የራእይ መጻሕፍት የሥነ ጽሑፍ ዐይነታቸውን ባገናዘበ መልኩ እንዴት ሊፈቱ እንደሚገባቸው ትንተና ቀርቦባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የአዲስ ኪዳን ታሪካዊና ማኅበራዊ መቼት አብሮ ተካትቷል። በእነዚህ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ ተመሳሳይ የሥነ ጽሑፍ ቅርጽ ያላቸው መጻሕፍት በአንድ ላይ በማድረግና የሥነ ጽሑፋዊ ቅርጽ ባሕርያትን በማጉላት ትንታኔ የቀረበበት ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ክፍል በምሳሌዎች የተሞላ ነው።

የመጨረሻው ምዕራፍ ስድስት፣ መጽሐፍ ቅዱስን በመፍታት ሂደት ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ሚና ምን እንደ ሆነ ውይይት የተደረገበት ነው። ይህንንም ለማሳየት “መገለጥ”፣ “አብርሆት” እና “ትርጓሜ” የሚሉ ቃላት ተብራርተዋል። መንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ሂደት ውስጥ ጥናትን እንደማይተካ ወይም እንደማይከለክል ተመላክቷል።

ብይን ስለ መጽሐፉ
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው፣ መጽሐፉ የወንጌላውያን አማኞችን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ትርጓሜን የተከተለ ቢሆንም፣ የኦርቶዶክሳውያንና የካቶሊካውያን ትርጓሜ ስልቶች በቂ ስፍራን አግኝተዋል። ይህ የመጽሐፍን አድማስና ተደራሽነት ከማስፋቱ በተጨማሪ፣ አንባቢያን ሥነ አፈታትን ሰፋ አድርገው እንዲመለከቱት ያስችላቸዋል። መጽሐፍ ቅደስ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት በተለያዩ ቤተ እምነቶች በመነበብ ላይ ያለ መጽሐፍ ነው፤ ስለዚህም ማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ ለዚህ የበለጸገ የትርጉም ባህል ዕውቅና መስጠት አለበት።

ሌላው የመጽሐፉ ብርቱ ጎን ዐውዳዊ መሆኑ ነው። ጸሐፊው መልእክቱን ተደራሽ ለማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የሥነ አፈታት መንገድ አቅርቦልናል። ይህም ሥነ አፈታትን ከምዕራባውያን የወረስነው ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዘመናት ሲተገበር የነበረ እንደ ሆነ የሚያስገነዝበን ነው። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥነ ጽሑፋዊ ቅርጽ በሚተነትንበት ክፍል ሥር፣ ለተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ቅርጽ ማሳያ ይሆኑን ዘንድ ብዙዎቻችን ከምናውቃቸውና አገር በቀል ጸሐፍት ከሆኑት ሥራዎች መካከል በመጥቀስ ሊያስረዳን ሞክሯል። እነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ዳኛቸው ወርቁና የመሳሰሉት እንደ ማሳያነት የቀረቡ ሥራዎች ናቸው።

መጽሐፉ በምርምር ላይ የተመሠረተና በጉዳዩ ላይ ሰፊ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ምሁራን ሥራዎች በስፋት ያጣቀሰ ነው። ይህ ደግሞ ጸሐፊው ለተለያዩ ዕይታዎች ክፍት እንዲሆን ብቻ ሳይሆን፣ የራሱን አቋም ከሌሎች ዕይታዎች ባንጻሩ በግልጽ እንዲያስቀምጥ አድርጎታል።

መጽሐፉ የቃላት መፍቻ እና የቃላት ማውጫ (Index) ተዘጋጅቶለት ቢሆን ኖሮ ለአንባቢያን የበለጠ ዕገዛ ያደርግ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ፣ አልፎ አልፎ የሚታዩ የፊደል ግድፈቶች ተስተውለዋል። በቀጣይ ዕትም እነዚህ እንከኖች ተስተካክለው እንደሚቀርቡ እምነቴ ነው። የመጽሐፉ የመጀመሪያ ዕትም በአሜርካን አገር የታተመና በአገር ቤት ገበያ ላይ የሌለ መሆኑ፣ ለሁሉም አንባቢያን እንዳይደርስ አድርጎታል። ስለሆነም ለአገር ቤት አንባቢያን በቶሎ የሚደርስበት መንገድ እንዲመቻች ዐደራን አስቀድሜ እጠይቃለሁ።

መጽሐፉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሥነ አፈታት ትምህርት መግቢያ መማሪያነት እንዲያገለግል ሆኖ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተዘጋጀ ነው። ሆኖም ግን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄና በኀላፊነት ማንበብ የሚፈልጉ ሁሉ ቢያነብቡት በእጅጉ ይጠቀማሉ።

ወንድማችን ምኒልክ አስፋው እንዲህ ዐይነት ሥራ ለንባብ በማቅረቡ በእጅጉ እያመሰገንሁ፣ ‘እንኳን ደስ አለህ!’ ልለው እወድዳለሁ። ሌሎቻችንም የእርሱን ፈለግ በመከተል በምርምር ላይ የተመሠረተ፣ ዐውዳዊ ገጽታ ያለው እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ መጽሐፍ እንድንጽፍ እግዚአብሔር ይርዳን።

ዳሠሣ አቅራቢ

Nebeyou Alemu (PhD)

ነቢዩ ዓለሙ፣ በትምህርት ዝግጅቱ በጥንታዊ መዛግብት ጥናት (Philology) የፒ.ኤች.ዲ ጥናቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያደረገ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ድኅረ ምረቃ ሥነ መለኮት ት/ቤት ማስተርስ ኦፍ ዲቪኒቲ ሠርቷል። በአሁኑ ጊዜ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ (UNISA) በሥነ መለኮት ሁለተኛ የፒ.ኤቺ.ዲ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል። በተለያዩ የሥነ መለኮት ት/ቤቶች የሚያስተምረው ዶ/ር ነቢዩ ዓለሙ፣ በዊክሊፍ ኢትዮጵያ የትርጉም ሥራ አማካሪ ነው። ታሪክ፣ ሃይማኖት እና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥናቶችን ማድረግ ያስደስተዋል።

Nebeyou Alemu

Want your school to be the top-listed School/college in Addis Ababa?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Category

Website

Address


Addis Ababa