22/06/2026
የቅሬታ ሰሚ አተገባበር እና ተግባራዊነትን በተመለከተ ለቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ስልጠና ተሰጠ፡፡
ደሴ፡- ሰኔ 15 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ)
በወይዘሮ ስኂና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የቅሬታ ሰሚ አተገባበር እና ተግባራዊነትን በተመለከተ ለኮሌጁ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስልጠናው በEASE (Education and Skill For Employability) ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀ ነው፡፡
ስልጠናውን የሰጡት የEASE ፕሮጀክት የአካባቢና ማህበራዊ ጥበቃ (Environment & Social Safeguard) አስተባባሪ እና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መላኩ መሃመድ ሲሆኑ፣ በፕሮጀክቱ ሂደት ውስጥ ቅሬታዎች ቢፈጠሩ ሊከተሉ ስለሚገባቸው የቅሬታ አፈታት (Grievance Redress Mechanism) ሂደቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አስተባባሪው አክለውም እስካሁን በፕሮጀክቱ ዙሪያ የተነሱ ቅሬታዎች ምን ምን እንደነበሩና በተግባር የተፈቱበትን ስኬታማ መንገድ ለኮሚቴው አባላት አስታውሰዋል፡፡
በስልጠናው ወቅት የስነ-ምግባር ደንብ፣የአካባቢ ጥበቃ ትኩረት እንዲሁም በEASE ፕሮጀክት አማካኝነት በስርዓተ-ፆታ ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ በተለይም በሴቶች አቅም ግንባታ ዙሪያ ወደፊት በርካታ ስራዎችን ለመስራት መታቀዱንም ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላቱ በEASE ፕሮጀክት ድጋፍ በኮሌጁ ግቢ ውስጥ ለሴት ሰልጣኞች ማረፊያና (Female Trainees Wellness center) የንፅህና መጠበቂያ እንዲያገለግሉ ተለይተው የተዘጋጁትን ክፍሎች በመዘዋወር ጎብኝተዋል፡፡
20/06/2026
የቅዳሜ ገበያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በስራና ተግባር ስርዓተ ትምህርት ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ፡፡
ደሴ፡- ሰኔ 13 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ)
የቅዳሜ ገበያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአዲሱ የስራና ተግባር ስርዓተ ትምህርት ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በድምቀት አስመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አብነው ደሳለኝ፤ የቀድሞው ስርዓተ ትምህርት ይዘት በጽንሰ-ሃሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ ተማሪዎችን ለፈጠራ የሚያነሳሳ እንዳልነበረ አስታውሰዋል። በአንጻሩ አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ከጽንሰ-ሃሳብ ባለፈ በተግባራዊ ልምምድ ላይ ትኩረት የሚያደርግ በመሆኑ ተማሪዎችን ለስራ ፈጠራ የሚያነሳሳና የሚያዘጋጅ ነው ብለዋል።
ርዕሰ መምህሩ አክለውም ተማሪዎቹ የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ከመርዳት ጀምሮ ለስልጠናው ስኬታማነት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማሟላት ድጋፍ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የደሴ ከተማ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ፍቅር አበበ በበኩላቸው፣ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተማሪዎች ገና ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ የሙያ ትምህርት እንዲወስዱ የሚያበረታታ በመሆኑ፣ የፈጠራ ችሎታና ክህሎት ላላቸው ተማሪዎች ትልቅ አጋዥና በር ከፋች መሆኑን አስገንዝበዋል። አቶ ፍቅር አያይዘውም ወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በከተማዋ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሙያ ትምህርቱ ውጤታማ ይሆን ዘንድ እያደረገ ላለው ከፍተኛ እገዛና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሌላው በምረቃው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ሰለሞን ይመር፣ ኮሌጁ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ያሳለፋቸውን የስኬት ጉዞዎች ያወሱ ሲሆን፤ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሰልጣኞችን በብቁ ክህሎትና እውቀት አንጸው "ከታዛዥነት ወደ አዛዥነት" (ወደ ስራ ፈጣሪነት) የሚቀይሩ መሆናቸውን አስረድተዋል። በመሆኑም ወጣቶች የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን ቀዳሚ ምርጫቸው እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ይህ በከተማዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የምረቃ ስነስርዓት ላይ የሙያ ትምህርት ስልጠና በአራት ዋና ዋና የስልጠና ዘርፎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ እነሱም፡ጋዜጠኝነት፣የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት፣አካውንቲንግና ፋይናንስ እንዲሁምኮምፒውተር ሳይንስ ናቸው፡፡
20/06/2026
በደሴ ከተማ በወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የአጫጭር ስልጠና ምረቃ ስነ-ስርዓት ተከናወነ፡፡
ደሴ፡- ሰኔ 13 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ)
የደሴ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከ «3R-4 CACE» ፕሮጀክት ጋር በመተባበር፣ በወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የስራ ክህሎት ዘርፎች ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ሴቶችና እናቶችን ዛሬ በድምቀት አስመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደሴ ከተማ አስተዳደር ገንዘብ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀሰን አበጋዝ ሰልጣኞቹ ከ10 እስከ 45 ቀናት በቆየው በዚህ ተግባራዊ ስልጠና ላይ በቂ እውቀትና ክህሎት መጨበጣቸውን ገልጸዋል። ይህ ያገኙት እውቀትም በቀጣይ ወደ ስራው ዓለም ሲገቡ ትልቅ አጋዥ ሊሆናቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ሰለሞን ይመር በበኩላቸው፣ ሰልጣኞቹ በቆይታቸው በቂ እውቀት እንዳገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ስልጠና ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው ፕሮጀክቱ ለስልጠናው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችንና ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ ያሟላ መሆኑ እንዲሁም ሰልጣኞቹ በሙሉ ሴቶች መሆናቸውና ስልጠናውን ደግሞ በሴት ባለውለታ ስም በተሰየመው አንጋፋው የወ/ሮ ስኂን ተቋም ውስጥ መከታተላቸው ልዩ ትርጉም እንዳለው ጠቁመዋል።
ዲኑ አክለውም፣ ኮሌጁ ስልጠና በመስጠት ብቻ እንደማይወሰንና ተመራቂዎቹ ወደ ስራ ከተሰማሩ በኋላም የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
ስልጠናው በግብርናው ዘርፍ፡ የዶሮ እርባታ፣ የፍየልና በግ እርባታ እንዲሁም እንስሳት ማድለብ፣ በአነስተኛ ማኑፋክቸሪንግና ኢንደስትሪ፡ የልብስ ስፌት እና የላርጎ (ፈሳሽ ሳሙና) ማምረት እንዲሁምበአገልግሎት ዘርፍ፡- የምግብ ዝግጅት ስልጠናዎች ይገኙበታል፡፡
ይህ በሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ እና በ «3R-4 CACE» ፕሮጀክት ትብብር የተካሄደው የስራ ክህሎት ስልጠና፣ የምረቃው ባለቤት የሆኑትን እናቶችና ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉና በከተማዋ ልማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
19/06/2026
በወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በEASE ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለሆኑ የትምህርት ክፍሎች የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና ተሰጠ፡፡
ደሴ፡- ሰኔ 12 / 2018 ዓ.ም (ወስፖኮ)
በወይዘሮ ስህና ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በEASE (Education and Skill For Employability) ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለሆኑ የትምህርት ክፍሎች የተዘጋጀ የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል። ይህ ስልጠና በዋናነት ለጋርመንት፣ ለኤሌክትሪክ ሲቲ እና ለአይሲቲ (ICT) የትምህርት ክፍሎች የተሰጠ ሲሆን፣ ዓላማውም ፕሮጀክቱ እየሰራቸው ያሉ ተግባራትን ግልጽ ለማድረግ ነው።
ስልጠናው በEASE ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ የተሰጠ ሲሆን የፕሮጀክቱ የአካባቢና ማህበራዊ ጥበቃ (Environment & Social Safeguard) አስተባባሪ የሆኑት አቶ መላኩ መሃመድ በስልጠናው ላይ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል። አስተባባሪው በንግግራቸው የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ዓላማና አተገባበር ያብራሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክቱ አማካኝነት እየተሰሩ ያሉ ዋና ዋና ስራዎችን ለተሳታፊዎች አብራርተዋል።
አቶ መላኩ አያይዘውም በፕሮጀክቱ ሂደት ውስጥ ቅሬታዎች ቢፈጠሩ ሊከተሉ ስለሚገባው የቅሬታ አፈታት ሂደት Grievance Redress Mechanism (GRM) እና ስለ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው አሰራር ዝርዝር መረጃ ሰጥተዋል። በተጨማሪም፡የስነ-ምግባር ደንብ፡ ፕሮጀክቱ የሚከተለውን ጥብቅ የስነ-ምግባር መመሪያ ፣ የስራ ላይ ስለሚደረግ የደህንነት አጠባበቅ Occupational Health and Safety (OHS)፣ ለአካባቢ ጥበቃ የሚሰጥ ትኩረት እንዲሁም በስራዎች ሳቢያ በአካባቢ ላይ የሚደርሱ ተጽእኖዎችን ለመቀነስ የተነደፉ ልዩ የአካባቢ ጥበቃ ስልቶችን በተመለከተ ሰፊ ግንዛቤ አስጨብጠዋል።
በተመሳሳይም በዕለቱ የፕሮጀክቱ የስርዓተ-ፆታ ፎካል (Gender Focal person) የሆኑት ወይዘሮ ገነት መላኩ በበኩላቸው በስርዓተ-ፆታ ዙሪያ Gender Based Violence(GBV)እና በEASE ፕሮጀክት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስመልክተው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ወይዘሮ ገነት በስልጠናው ወቅት በሴቶች አቅም ግንባታ፣ በፕሮጀክቱ ድጋፍ በኮሌጁ ግቢ በሴቶች ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ያሉትን ስራዎች አንስተዋል።
ይህ የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና በኮሌጁ የEASE ፕሮጀክት ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ፣ ግልጽነት የተሞላባቸው እና ማህበራዊና አካባቢያዊ ኃላፊነትን ያገናዘቡ እንዲሆኑ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ይታሰባል፡፡
16/06/2026
የሴቶችና እናቶችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያለመ የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
ደሴ፡-ሰኔ 9 /2018ዓ.ም (ወስፖኮ)
በደሴ ከተማ የሴቶችና የእናቶችን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ ያለመ የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ ስልጠናው የ3R-4 ፕሮጀክት ከወይዘሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፣ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሴቶች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
ስልጠናው በግብርናው ዘርፍ፡ የዶሮ እርባታ፣ የፍየልና በግ እርባታ እንዲሁም እንስሳት ማድለብ፣ በአነስተኛ ማኑፋክቸሪንግና ኢንደስትሪ፡ የልብስ ስፌት እና የላርጎ (ፈሳሽ ሳሙና) ማምረት እንዲሁምበአገልግሎት ዘርፍ፡- የምግብ ዝግጅት ስልጠናዎች ይገኙበታል፡፡
ይህ እንደየዘርፉ ባህሪ ከ10 እስከ 45 ቀናት የሚቆይ የክህሎት ስልጠና፣ እናቶችና ሴቶች ራሳቸውን ችለው ወደ ስራ እንዲገቡና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
12/06/2026
በወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የሙያ ብቃት ምዘና በመሰጠት ላይ ነው
ደሴ፡-ሰኔ 5 /2018ዓ.ም (ወስፖኮ)
10/06/2026
ለወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ሰራተኞች የISO 9001:2015 የጥራት አመራር ስርዓት እና የውስጥ ጥራት ኦዲትን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ::
ደሴ፡-ሰኔ 3 /2018ዓ.ም (ወስፖኮ)
የወይዘሮ ስኂን ፖቴክኒክ ኮሌጅ የISO 9001:2015 የጥራት ስራ አመራር ስርዓትን አስመልክቶ ለሰራተኞች የተዘጋጀ የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና ተሰጠ፡፡
ስልጠናው Education and Skill for Employment Project (EASE) ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት የሚሰጥ ነው፡፡
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኮሌጁ ዲን አቶ ሰለሞን ይመር እንደገለጹት የዚህ ስልጠና ዋና ዓላማ ሰራተኛው ተቋማዊ የጥራት መርሆዎችን ጠብቆ እንዲሰራ ለማንቃትና ለማስታወስ ነው፡፡ ኮሌጁ በበጀት ዓመቱ ለሚጠብቀው ዓለም አቀፍ የክትትል ኦዲት (Surveillance Audit) ብቁ ዝግጅት ማድረግ እንዲችል የሰራተኛው ግንዛቤ መታደስ ወሳኝ መሆኑንም ዲኑ አክለው ገልጸዋል፡፡
ይህ ስልጠና ተቋማችን ቀደም ሲል ያገኘውን የISO 9001:2015 ዕውቅና ይዞ ለመቀጠልና ለሚመጣው የክትትል ኦዲት ራሱን በሚገባ ለማዘጋጀት ትልቅ ዕድል ነው ያሉት አቶ ሰለሞን ሰራተኛው ከዚህ በፊት የነበረውን ግንዛቤ በማደስ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መሙላት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ሰልጣኝ ስልጠናውን በትኩረትና በሃላፊነት ስሜት ሊከታተለው እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ስልጠናው በውስጥ ጥራት ቁጥጥር ክፍል የተሰጠ ሲሆን ከISO 9001:2015 የጥራት አመራር ስርዓት በተጨማሪ ሶስት ማንዋሎች ላይ ማለትም ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የጥራት ማረጋገጫ መስፈርቶች መመዘኛና መገምገሚያ ማንዋል ፣ሱፐርቪዥንና ኢንስፔክሽን እንዲሁም ዲጂታል ላይብረሪ የሚሉት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
08/06/2026
የወ/ሮ ስኂን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በአይሲቲ የስልጠና ዘርፍ የሚሰለጥኑ የ2018 ዓ.ም የቀን ተመራቂ ተማሪዎች የሰሩትን የተለያዩ ፕሮጀክት ለመምህራቸው ገለፃ ሲያደርጉ የሚያሳይ ምስል፡-